ድሬዳዋ ላይ የሚደረገውን የድሬዳዋ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ተስተካካይ ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከሦስት ተጫዋቾች በላይ በማስመረጡ ከሁለተኛው ሳምንት የተላለፈው ይህ ጨዋታ ባለሜዳው ድሬዳዋ ከሐረር የሚለስበት የመጀመሪያ ጨዋታው ይሆናል። የመጫወቻ ሜዳቸው ዕድሳታ የተጠናቀቀላቸው ድሬዎች በመጨረሻው የሐረር ጨዋታቸው ሣምንት በፋሲል ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ቡድኑ ዘንድሮም ወጥ አቋም ማሳየት ያልቻለ ሲሆን በአራት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከተጋጣሚው እጅግ በባሰ ሁኔታ ላይ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስም በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው በባህር ዳር ከተማ መረታቱ የሚታወስ ነው። በተስተካካይነት የነገው ጨዋታ ብቻ እጃቸው ላይ የቀረው ደቡብ ፖሊሶች ከአራት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ 16ኛ ደረጃን ይዘው ወደ ምስራቋ ከተማ አምርተዋል።
አምስት የሚደርሱ ተጫዋቾቻቸው ላይ ጉዳት የነበሩባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ለነገው ጨዋታ ከራምኬል ሎክ እና ወሰኑ ማዜ ውጪ ያለው ስብስባቸው ዝግጁ መሆኑ ታውቋል። በደቡብ ፖሊስም በኩል በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩን ብርሀኑ በቀለ ብቻ ሆኗል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከሽንፈት እንደመምጣታቸው ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ለማግኘት በማሰብ የጨዋታ ዕቅዳቸውን እንደሚያወጡ ይገመታል። በተለይም ድሬዳዋ ከተማዎች ማጥቃትን መሰረት ያደረገ እና የመስመር አማካዮቻቸውን ተሳትፎ የሚሻ አቀራረብ ይዘው ሊቀርቡ ይችላሉ። በመሆኑም ቡድኑ ከፊት ለሚያሰልፈው የሁለት አጥቂዎች ጥምረት የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር ከቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶች ባለፈ ለተጋጣሚ የአደጋ ክልል ከሚቀርቡት የመስመር አማካዮቹ እና በአጥቂዎቹ መካከል በሚደረጉ ቅብብሎች እንደሚያጠቃ ይገመታል። የመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ በርካታ ለውጦችን እንደሚያደርጉ በሚጠበቁት ደቡብ ፖሊሶች በኩል ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ሊኖር ቢችልም ግብ ካስቆጠረ የቆየው የፊት መስመር የሦስትዮሽ ጥምረታቸው ከመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የድሬን የኋላ መስመር ለመፈተን እንደሚችል ይታሰባል። ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች በተለይም እንግዶቹ ደቡብ ፖሊሶች ግብ ካገኙ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸው የሚቀር አይመስልም።
የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች ከ2002 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን እስካሁን እርስ በእርስ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ አንዴ ድል ቀንቶት አንዱ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
– በአራቱ ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ስቆጠሩ አራቱ በድሬዳዋ አራቱ ደግሞ በደቡብ ፖሊስ የተመዘገቡ ናቸው።
– ድሬዳዋ ላይ ሁለት ጊዜ የተገናኙባቸው ጨዋታዎች በባለሜዳዎቹ የ1-0 እና የ3-2 አሸናፊነት ተጠናቀዋል።
– ደቡብ ፖሊስ ዘንድሮ በመከላከያ 2-1 ከተረታበት ጨዋታ ውጪ የተሸነፈባቸው ሌሎች አራት ጨዋታዎች በሙሉ በ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። ቡድኑ ደደቢትን ከረታ በኋላም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖታል።
– በሊጉ መጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቻቸው ሦስት ግቦችን ያስቆጠሩት ድሬዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቻቸው ግን ግብ አልቀናቸውም።
– ደቡብ ፖሊስ በመከላከያ 2-1 ከተረታበት ጨዋታ ውጪ የተሸነፈባቸው ሌሎች አራት ጨዋታዎች በሙሉ በ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። ቡድኑ ደደቢትን ከረታ በኋላም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖታል።
– በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቻቸው ሦስት ግቦችን ያስቆጠሩት ድሬዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎቻቸው ግን ግብ አልቀናቸውም።
ዳኛ
– ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የሚመራው ፌደራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ ነው። አክሊሉ ከባህር ዳር እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ተጥሎ ሁለተኛ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ይዳኛል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)
ሳምሶን አሰፋ
ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሃንስ
ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ – ምንያህል ይመር – ሲላ አብዱላሂ
ኢታሙና ኬይሙኒ – ኃይሌ እሸቱ
ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)
ዳዊት አሰፋ
አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ
ኄኖክ አየለ – ኤርሚያስ በላይ – ሙሉዓለም ረጋሳ
መስፍን ኪዳኔ – በኃይሉ ወገኔ – ብሩክ ኤልያስ