ከፍተኛ ሊግ | የአራተኛ ሳምንት ምድብ ሀ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ተከናውነው ወልዲያ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ ሲጥሉ ለገጣፎ በአሸናፊነቱ ገፍቶበታል።

ባህር ዳር ላይ ለገጣፎ ለገዳዲን ያስተናገደው አውስኮድ 1-0 ተሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተዳክመው የታዩ ሲሆን የጠራ የግብ ማግባት ሙከራዎችንም ቡድኖቹ ለማስመልከት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በ7ኛው ደቂቃ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ የተስተናገደ ሲሆን በተጋባዦቹ ለገጣፎዎች በኩል የተደረገ ነበር። ዳዊት ቀለመወርቅ በቅጣት ምት አማካኝነት ኳሷን ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረት አድርጎ ሳይሳካ ቀርቷል። የግብ ማግባት ሙከራ ድርቅ የነበረበት ይህ የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ከዚህኛው አጋጣሚ በኋላ ሙከራ ለማስተናገድ 30 ደቂቃዎችን መጠበቅ ግድ ብሎታል። ከ35ኛው ደቂቃ በኋላ በተሻለ ለማጥቃት የተንቀሳቀሱት ባለሜዳዎቹ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በ36ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ በዓለምላይ ሞትባይኖር ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ በማድረግ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ኳሱ የግቡን የውጪ መረብ ነክቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። በደቂቃ ልዩነት ታሪኩ ጎጀሌ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ የመታው ኳስ መረብ ላይ ለማረፍ የተቃረበ ቢመስልም የግቡ ቋሚ መልሶታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃው ለገጣፎዎች በነስረዲን ኃይሉ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው የነበረ ቢሆንም ደረጄ ዓለሙ ኳሱን ተቆጣጥሮት ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የመጡት ተጋባዦቹ በርካታ እድሎችን በመፍጠር ተሽለው ተንቀሳቅሰዋል። በተቃራኒው ከመጀመሪያው አጋማሽ የባሰ ተዳክመው የተጫወቱት አውስኮዶች ከተጋጣሚያቸው የሚሰነዘርባቸውን ጫና እንኳን መቋቋም ተስኗቸው ታይተዋል። ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ለገጣፎዎች ከቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር በመሞከር ቀዳሚ ለመሆን ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። እየተፍረከረከ የመጣውን የአውስኮድ የተከላካይ መስመር በአየር ላይ ኳሷች ለማሸነፍ በሚመስል መልኩ ለገጣፎዎች የአየር ላይ ኳሶችን ሲያዘወትሩ የነበረ ሲሆን በ52ኛው ደቂቃም በሳዲቅ ተማም አማካኝነት ጥሩ እድል አግኝተው አምክነዋል። አሁንም ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት ለገጣፎዎች በመክብብ ወልዴ የርቀት ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ደረጄ ዓለሙ አውጥቶባቸዋል። ደረጄ ወደ ውጪ ያወጣውን ኳስ ለገጣፎዎች ከመዓዘን አሻምተውት በ66ኛው ደቂቃ በሳዲቅ ተማም የግምባር ኳስ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል።

ግብ ማስቆጠራቸው የልብ ልብ የሰጣቸው በሚመስል መልኩ ተጋባዦቹ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉ ሲሆን በ71ኛው እና በ79ኛው ደቂቃ በሽመክት ግርማ እና በሐብታሙ ፈቃደ አማካኝነት ተጨማሪ ጎሎች ለማስቆጠር የሚችሉበት አጋጣሚዎች ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። ሰዓት እያለቀ ሲሆድ ባለሜዳዎቹ ከጨዋታው አንድ ነጥብ እንኳን ይዞ ለመወጣት ቢሞክሩም የለገጣፎዎችን የተከላካይ መስመር ጥሰው መግባት ግን ተስኗቸው ታይቷል። አውስኮዶች በ85ኛው እና በ87ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ሙክታር ሐሰን አማካኝነት ያለቀለት የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በለገጣፎዎች 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከማሸነፍ ርቆ የቆየው የሻምበል መላኩ ቡድን ወሎ ኮምበልቻ የአመቱን የመጀመሪያ ድል በቡራዩ ከተማ ላይ አሳክቷል። ለወሎ ኮምቦልቻ ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው በ32ኛው ደቂቃ ነቢዩ አህመድ ነው።

ሶስት ተከታታይ ጨዋታ አቻ የተለያየው ፌዴራል ፖሊስ በዓመቱ የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል። አዲስ አዳጊው አቃቂ ቃሊቲን 1-0 ማሸነፍ ለቻለው ፌደራል ፖሊስ በ87ኛው ደቂቃ ላይ አስተዋይ ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠር ቸሏል።

ወልዲያ ላይ ደሴ ከተማን ያስተናገደው ወልዲያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። ዐቢይ ቡልቲ በ~7ኛው ደቂቃ ወልዲያን ቀዳሚ አድርጎ ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ቢችልም ቻላቸው መንበሩ በሁለተኛው አጋማሽ ደሴን አቻ አድርጓል።

ከመሪዎቹ ተርታ የነበረው ሌላው ቡድን ኤሌክትሪክ ከ ሰበታ ከተማ ያደረገውን ጨዋታ ያለ ጎል ሲደመደምም ወደ አክሱም ያመራው አዲስ አዳጊው ገላን ከተማ 1-0 አሸንፎ ተመልሷል።

የመጀመርያ አምስት ደረጃ የያዙ ቡድኖች

1. ለገጣፎ 4 (+3) 10
2. ወልዲያ 4 (+2) 8
3. ኤሌክትሪክ 4 (+2) 8
4. ፌዴራል ፖሊስ 4 (+1) 6
5. ሰበታ ከተማ 4 (+1) 6