የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሙሉ እሁድ ተከናውነው ሀምበሪቾ፣ ኢኮስኮ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ሀላባ ከተማ ድል ማግኘት ችለዋል።
ያያ ቪሌጅ ላይ አአ ከተማን ከመድን ያገናኘው ጨዋታ በፈጣን የኳስ እንቅቃሴ እና የአካል ንኪኪ ታጅበ ተካሂዶ በመድን አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ፊት ገፍተው መጫወት የቻሉት መድኖች በ3ኛው ደቂቃ በሚካኤል ለማ አማካኝነት ለግብ ሲቀርቡ በ11ኛው ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ በግንባሩ ያደረገው የግብ ሙከራም ተጠቃሽ ነበር። ከ15 ደቂቃዎች በኋላ የሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን በቀጣይ ደቂቃዎች ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ያልታየበት፤ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል ለመድረስ የሚደርጉት እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጥ የተስተዋለበት ነበር። ሙሀጅር መኪ በ31ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሞክሮ በግቡ አናት የሄደችበት አጋጣሚ በአዲስ አበባ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
ከዕረፍት መልስ በተመሳሳይ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ቀጥሎ ለረጅም ደቂቃዎች የጎል ሙከራዎች ያልታዩ ሲሆን በ70ኛው ደቂቃ ሰለሞን ወዴሳ በግምት 30ሜትር ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት በመምታት መድንን አሸናፊ ማድረግ ያስቻለ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት በመድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መድን ሜዳ ላይ ኢኮስኮ ድሬዳዋ ፖሊስን አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ ምድቡን መምራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ለኢኮስኮ አቤኒዜር ኦቴ በ11ኛው ደቂቃ እንዲሁም ከአቻነት ውጤት ወደ አሸናፊነት የለወጠቻውን ግብ በ84ኛው ደቂቃ ኢሳይያስ ታደሰ አስቆጥረዋል።
ዱራሜ ላይ በዘካራያስ ፍቅሬ ሁለት ግቦች እና ተስፋሁን ተሰማ አንድ ግብ ተጋጣሚያቸውን የካ ክፍለ ከተማን 3-1 ማሸነፍ የቻሉት ሀምበሪቾዎች በነጥብ ከኢኮስኮ ጋር አቻ በመሆን በግብ ልዩነት ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ወልቂጤን ያስተናገደው ሀላባ ከተማ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። 1-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ የብቸኛዋ የድል ጎል ኤፍሬም ቶማስ (32ኛው ደቂቃ) ነው።
ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሲሜንት ከዲላ ከተማ ረፋድ 4:00 ላይ ባደረጉት ጨዋታ ናሽናል በ18ኛው ደቂቃ አድኖ ተመስገን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።
ወላይታ ሶዶ ከነገሌ አርሲ 1-1 የተለያዩበት ጨዋታ በሳምንቱ በዚህ ምድብ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ብቸኛ ጨዋታ ሆኗል።
የመጀመርያ አምስት ደረጃ የያዙ ቡድኖች
1. ኢኮስኮ 4 (+6) 10
2. ሀምበሪቾ 4 (+5) 10
3. መድን 4 (+5) 9
4. ሀላባ ከተማ 4 (+2) 8
5. ወልቂጤ 3 (+1) 6