ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ አራተኛ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች መካከል አምስቱ ዛሬ ተከተናውነው ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተከታታይ ድል በኋላ ነጥብ ሲጥሉ ከፋ ቡና እና ነገሌ ቦረና አሸንፈዋል።
ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን በሜዳው አስመዝግቧል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው እቅስቃሴ በሁለቱሕ ቡድኖች በኩል በአመዛኙ ኃይል የተቀላቀለበት ሲሆን የጎል ሙከራዎችም ሆነ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ መመልከት አልተቻለም፡፡ ባለሜዳዎቹ መከላከል ላይ ባመዘነ መልሶ ማጥቃት እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች በሚፈጥሯቸው እድሎች በአባ ቡናዎች ላይ ጫና ማሳደር ችለዋል። በ14ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ አዳነ ዓለሙ ሞክሮ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወደ ውጭ የወጣበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበር። በ30ኛው ደቂቃ በድጋሚ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ የአባ ቡና ተከላካዮች ተረባርበው ቢያወጡትም ከቀኝ ከሳጥን ጠርዝ አዳነ ዓለሙ አክርሮ በመምት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ካፋ ቡናን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ በጅማ አባቡና በኩል አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም በመስመር በኩል ፉዓድ ተማም በግል ከሚያደርጋቸው እቅስቃሴዎች ውጭ የጎላ እቅስቃሴም አልነበረም። እንዲሁም ቡድኑ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ኳስን ማደራጀት የተሳካ ቅብብሎሽ ሲሳናቸው በተጨማሪም ለተከላካዮች ሽፍን መስጠት ሲቸገሩ ተስተውለዋል። ለዚህም አጥቂው ካርሎስ ዳምጠው ብቻውን ተነጥሎ በካፋ ተከላካዮች መሀል አሳልፏል፡፡
ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ እንዲሁም በጎል ሙከራ የተሻሉት ጅማዎች በ49 እና 51ኛ ደቂቃዎች በፉአድ ተማም በኩል ከርቀት እንዲሁም በአንድ ሁለት ቅብብል ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ከፋ ቡናዎች እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ከቆሙ ኳሶች የሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች ወደ ግብነት አይቀየሩ እንጂ በተደጋጋሚ የአባቡናን ተከላካዮች ሲፈትኑ ነበር። በ53ኛው፣ 55ኛው፣ 57ኛው እንዲሁም በ71ኛው ደቂቃ በካሣዬ በቀለ፣ በአኒ አጁሉ እና በአዳነ ዓለሙ ተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ አስደንጋጭ ሙከራዎች ቢደረጉም ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም። በ62ኛው ደቂቃ የካፋ ቡናው አድማሱ ጌትነት በደረሰበት ከባድ የትከሻ ጉዳት በአምቡላንስ ወደ ህክምና መስጫ ተወስዷል። የዕለቱ ዳኛ ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ አደገኛ አጨዋወቶችን መፍቀዳቸው ከዚህም የከፉ ጉዳቶች ሊደርሱ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የባለሜዳው ደጋፊዎች በከባድ መኪናዎች ደስታቸውን ለመግለፅ መጫወቻ ሜዳ ላይ መግባታቸው እንዲሁም ቡድናቸውን ለመደገፍ ከጅማ ወደ ቦንጋ ተጉዘው የመጡ በርካታ የአባ ቡና ደጋፊዎች በቡድናቸው አቋም ደስተኛ ባለመሆናቸው ከቡድኑ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው አግራሞትን አጭሯል፡፡
ሌሎች ጨዋታዎች
ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከአርባምንጭ ከተማ 1-1 ተለያይተዋል። ወራቤዎች በጨዋታው መጀመርያ ባስቆጠሩት ጎል ረጅም ደቂቃዎች መምራት ቢችሉም ስንታየሁ መንግስቱ በ66ኛው ደቂቃ ለአርባምንጭ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ቦረና ላይ ነገሌ ቦረና ነቀምትን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። እንግዳው ቡድን ነቀምት ከተማ በ21ኛው ደቂቃ ቦኒ ቦቃ ባስቆጠረው ግብ መምራት ቢችልም ነገሌ በ35ኛው ደቂቃ በእስጢፋኖስ የኔጌታ ጎል አቻ ሆኗል። ከእረፍት መልስ የነቀምቱ እስራኤል ታደሰ የነገሌ ቦረና ቡድን ተጫዋችን በማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን በዚህም ምክንያት ጨዋታው ለ10 ደቂቃዎች ተቋርጦም ነበር። በ78ኛው ደቂቃ ለነገሌ ቦረና እና ለራሱ ሁለተኛውን ግብ እስጢፋኖስ የኔጌታ አስቆጥሮ ጨዋታው በነገሌ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቆል::
ሻሸመኔ ላይ ሀድያ ሆሳዕና ያለ ግብ አቻ ሲለያዩ ቤንጂ ማጂ ከ ሺንሺቾ ያደረጉት ጨዋታም በተመሳሳይ ያለ ግብ ተጠናቋል። በዚህ ጨዋታ ላይ ከሁለቱም ቡድን የቀይ ካርድ የታየ ሲሆን ስለ ጨዋታው የቤንች ማጂ ቡናው ቡድን መሪ አስተያየቱን ተሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል። ” እውነት ለመናገር የነበረው ዳኝነት ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አንዱ እና ትልቁ ነገር ነው። ለሁለታችንም የማይጠቅም ነገር ነው ያደረገው። ውድድሩ በጣም ፈታኝ በሆነበት በዚህ ጊዜ የሚመደቡ ዳኞች አትኩሮት ይሻቸዋል። በተለይ የተጋጣሚያችን ግብ ጠባቂ ላይ የተሰጠው ቀይ ካርድ ሰዓት አባክነሀል በሚል ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ወይም ሁለት ደቂቃ ላይ ነው። የእለቱ ኮሚሽነር ይህን ነገር ምን ብሎ እንደሚያው አላውቅም። ሰው ሆኖ ፍፁማዊ የለም፤ የዳኞች ኮሚቴ ጉዳዩን በአንፅንኦት ቢያየው ስንል ነው የምንጠይቀው” ብሏል።