በሰባተኛው ሳምንት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው መከላከያ በአስደናቂ የሁለተኛ አጋማሽ ብቃት 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደው መከላከያ ጎንደር ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ቡድኑ ውስጥ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞን በይድነቃቸው ኪዳኔ ከመተካቱ በቀር ሌላ ለውጥ ሳያደርግ ለዛሬው ጨዋታ የቀረበ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ግን በርካታ ለውጦች ተደርገዋል። በዚህም ሳምንት ደቡብ ፖሊስን ካሸነፈው የድቻ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተከላካይ መስመር ላይ ዐወል አብደላ በሙባረክ ሽኩር ፤ አማካይ መስመር ላይ ኄኖክ ኢሳያስ እና ፀጋዬ አበራ በፍፁም ተፈሪ እና ቸርነት ጉግሳ እንዲሁም ከፊት አንዱአለም ንጉሴ በባዬ ገዛኸኝ ተተክተዋል።
ጥሩ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ድቻዎች አጥቅቶ የመጫወት ዕቅድ እንዳላቸው ያሳዩት ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ነበር። በዓብዱልሰመድ ዓሊ መሪነትም በአጫጭር ቅብብሎች በተለይም የመከላከያን የቀኝ መስመር በተደጋጋሚ ለማጥቃት ሲሞክሩ ይታይ ነበር። መከላከያዎችም የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን መልሰው ለማሸነፍ በመጣር ወደፊት ገድፍቶ ለመሄድ ይጥሩ የነበሩባቸው አጋጣሚዎች መታየታቸው አልቀረም። ነገር ግን የሁለቱም ቡድኖች ሙከራዎች ከርቀት የምደትረጉ እና ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሆነው ቆይተዋል። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራም 14ኛው ደቂቃ ላይ በዳዊት እስጢፋኖስ ከሳጥን ውጪ የተመታ ኳስ የተገኘ ነበር። ሙከራውን ታሪክ ጌትነት በአግባቡ ማዳን ሳይችል ቀርቶ ፍቃዱ ዓለሙ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።
ምንም እንኳን መከላካያዎች ከአንድ ደቂቃ በኋላ በዳዊት ማሞ ከርቀት ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የሆኑት ለማጥቃት ከመሞከር ያልቦዘኑት ድቻዎች ነበሩ። 17ኛው ደቂቃ ከመሀል የተላከለትን ኳስ ይዞ ከተከላካዮች ጀርባ በመግባት ከይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር የተገናኘው ባዬ ገዛኸኝ መረጋጋት በተሞላበት አጨራረስ ድቻን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ፊት ገፍቶ በመጫወቱ የተቀዛቀዘ ወላይታ ድቻን እና ወደ ተጋጣሚው የሜዳ ክልል የማይዘል የኳስ ቁጥጥርየበላይነትን የያዘ መከላከያን ተመልክተናል።
የጦሩ የአማካይ መስመር ተጫዋቾች ለተከላካይ ክፍላቸው በቂ ሽፋን ይሰጡ የነበሩት ድቻዎችን አልፎ የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥር ኳስ ማመቻቸት ባለመቻላቸው በቀጥታ ወደ ፊት ወደሚሻገሩ ኳሶች አመዝነው ታይተዋል። ሆኖም በሜዳቸው መቅረትን የመረጡት ድቻዎች አልፎ አልፎ ከርቀት ከተደረጉባቸው ሙከራዎች ውጪ እምብዛም አልተጨነቁም። ይልቁኑም የወላይታ ድቻዎች ድንገተኛ መልሶ ማጥቃቶች ወደ ሙከራነት ለመለወጥ የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል። ከነዚህም መካከል 31ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር አማካዩ እዮብ ዓለማየሁ ከረጅም ርቀት በደረሰው ኳስ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ምንተስኖት ደርሶ ያስጣለው አጋጣሚ ይጠቀሳል። በአንፃሩ መከላከያዎች 41ኛው ደቅቃ ላይ ሽመልስ ተገኝ በኃይሉ ግርማ ያበረደለትን ኳስ ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት ነበር የተሻለው ሙከራቸው። ቡድኑ ወደ መጨረሻ ላይ በፈጠረው ጫናም ሦስት ተከታታይ የማዕዘን ምቶች ቢያገኝም ወደ ሙከራነት ሳይቀይራቸው ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ሚዛን ሙሉ ለሙሉ ፍፁም ገብረማርያምን እና ተመስገን ገብረኪዳንን በዳዊት ማሞ እና ፍቃዱ ዓለሙ ቀይረው ወዳስገቡት መከላከያዎች ያደላ ነበር።
48ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ሞክሮቶት የተደረበ ኳስ አግኝቶ እዮብ በድጋሜ መትቶ ኢላማውን በሳተበት አጋጣሚ የሁለተኛ አጋመሹን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት ድቻዎች በመከላከያ ተደጋጋሚ ጥቃት ከሜዳቸው ለመውጣት በእጅጉ ተቸግረው ታይተዋል። የጦና ንቦቹ 52ኛው ደቂቃ ላይ ከዳዊት የተሳሳተ ቅብብል በስነዘሩት መልሶ ማጥቃት እዮብ ከይድነቃቸው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በግብ ጠባቂው አናት ላይ የሰደዳት ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ከወጣች በኋላም ሌላ ሙከራ ለማድረግ ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል።
እጅግ ተነቃቅተው በተለይም ከፍፁም እና ምንይሉ ጀርባ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በታየው ተመስገን ልዩ ብቃት ታግዘው ከፍተኛ ጫና የፈጠሩት መከላከያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ በድቻ የግብ ክልል ዙሪያ በቅብብሎቻቸው አስጨናቂ ሆነው ታይተዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ካነሳው የማዕዘን ምት ፍፁም ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ታሪክን አልፎ ተከላካዮች ተረባርበው ነበር ከግቡ መስመር ላይ ያወጡት። ከአንድ ደቂቃ በኋላ በድጋሜ መከላከያዎች በቀኝ መስመር በሰነዘሩት ጥቃት ምንይሉ ከዳዊት የተቀበለውን ኳስ አክርሮ ሞክሮ ታሪክ አድኖበታል። የቡድኑ ጫና ቀጥሎም በ74 ኛው ደቂቃ ተመስገን የድቻን የመከላከል መስመር መሀል ለመሀል ሰብሮ የገባውን ኳስ አቀብሎት ፍፁም በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይርታል። ጎሏ መከላከያን አቻ ያደረገች ብቻ ሳትሆን ክለቡ ከድቻ ጋር ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በኋላ ያስመዘገባትም ብቸኛ ጎል ነበረች።
ከግቡ በኋላም የመከላከያዎች ጫና አልበረደም። 68ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ሳጥን ውስጥ ከምንይሉ ተቀብሎ የመታውም ኳስ ከባድ ሙከራ የነበረ ቢሆንም ታሪክ አድኖታል። ሆኖም መከላከያዎች መምራት የቻሉበት አጋጣሚ መፈጠሩ አልቀረም። 74ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከዳዊት የተቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥን ውስጥ ይዞ ሲገባ የግራ መስመር ተከላካዩ ኄኖክ አርፌጮ በሰራበት ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ ከመረብ አገናኝቶ መከላከያን መሪ አደረገ። ከዚህ በኋላ ወደ ማጥቃት መንፈሳቸው ለመመለስ ጥረት የጀመሩት ድቻዎች እንዳሰቡት ብልጫ ከመውሰዳቸው በፊት ሌላ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። የግቧ አስቆጣሪ ምንይሉ ወንድሙ ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በቀኝ መስመር ወደ ድቻ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ አክርሮ በመምታት ነበር የታሪክ መረብ ላይ ያዋኃዳት።
ድቻዋች መጠነኛ መነቃቃት ቢያሳዩም 84ኛው ደቂቃ ላይ ካመከኑት እጅግ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ በኋላ ሌላ ዕድል አልፈጠሩም። በሙከራው እሸቱ መና ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ የተቆጣጠረው እዮብ ከግቡ አፋፍ ላይ የጦሩን ተከላካዮች በአስደናቂ የቴክኒክ ብቃት ጥሎ ቢሞክርም ለቡድኑ በሚያስቆጭ መልኩ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ይህ ኳስ ሲሳት ስድስት የሚደርሱ የድቻ ተጫዋቾች መሬት ላይ ወድቀው ቁጭታቸውን ስገልፁ ታይተዋል። ጨዋታውም የውጤት ለውጥ ሳይታይበት በመከላከያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።