ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ደረጃውን አሻሽሏል 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ በሆነውና በአዲስ አበባ ስታዲየም ጥሩ ሰሞነኝ ብቃት ላይ ይገኝ የነበረው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ከኢትዮጵያ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አዳማ ከተማን 1ለ0 ከረታው ቡድን ውስጥ ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱን በሚኪያስ መኮንን ብቻ ተክተው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ በአንጻሩ ወልዋሎዎች ደግሞ ደደቢትን ከረታው ስብስባቸው ውስጥ አማኑኤል ጎበናን አስወጥተው አስራት መገርሳን ብቻ በማስገባት ለጨዋታው መቅረብ ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች ፍፁም የበላይ በነበሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ገና ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ጫና ፈጥረው በመጫወት በ4ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሀንስ ከማእዘን የተሻማ ኳስ ተገጭቶ ሲመለስ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ቡናዎች በዚሁ አጋማሽ ከአዳማው ጨዋታ ጋር ተመሳሳይ በሚባል መልኩ በርካታ የቅብብል ስህተቶች በተለይም በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ የተወሰደባቸው ወልዋሎዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ አሻሞ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ አክርሮ የመታውና ዋቴንጋ በቀላሉ ካዳነበት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል ጥቃት መሰንዘር ሳይችሉ ቀርተዋል። በእንግዶቹ በኩል እንደ ጠንካራ ጎን ሊነሳ የሚችለው አስራት መገርሳና ብርሃኑ አሻሞ ለተከላካዮቻቸው በቂ የሆነ ሽፋን በመስጠት የኢትዮጵያ ቡናን መሀል ለመሀል ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን መመከታቸው እንዲሁም ከቀሪው የቡድኑ ተጫዋቾች ከተነጠሉት ሶስት አጥቂዎች መካከል ሪችሞንድ አዶንጎ በግሉ የመጀመሪያ ኳሶችን ለማሸነፍ የሚያደርገው ጥረት ብቻ ነበር፡፡

ሱሌይማን ሉክዋ እንደ አዳማው ጨዋታ ሁሉ ባለው ደካማ የሆነ ውሳኔ አሰጣጥ ብቃት የተነሳ በ7ኛው በ23ኛው እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሶስት እጅግ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎችን አምክኗል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ተካልኝ ደጀኔ ከማእዘን ያሻማትን ኳስ ተመስገን ካስትሮ ሸረፍ አድርጎ ወደ ግብ ልኳት የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችው በ29ኛው ደቂቃ ሚኪያስ ሁለት የወልዋሎ ተከላካዮችን አልፎ ለአብበከር ናስር አቀብሎት አብበከር በማይታመን ሁኔታ ያመከናት ኳሶችም ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ ቢያንስ ሁለት ለዜሮ እየመራ ሊወጣ የሚችልባቸው እድሎች ነበሩ፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ለማግባት ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ፍላጎትን ይዘው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። ይህም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ58ኛው ደቂቃ ቢኒያም ሲራጅ ሚኪያስ መኮንን ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ነስሩ በአግባቡ በመጠቀም አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ከዚች ግብ መቆጠር በኋላ የጨዋታው መልክ ሙሉ ለመሙሉ በሚያሰኝ መልኩ ተለውጧል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግቧ መቆጠር በፊት የነበራቸውን የማጥቃት ፍላጎት አጥተው ጥንቃቄን ምርጫቸው በማድረግ ወደ ኃላ በማፈግፈግ በቀጥተኛ አጨዋወት አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ለመፍጠር ሞክረዋል ፤ ያደረጓቸው ቅያሬዎችም ይህንን የሚያሳዩ ነበሩ። በ83ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ሉክዋ ካደረገው ሙከራ በስተቀርም ተቀዛቅዘው ተስተውለዋል፡፡

በአንጻሩ በቀሩት ደቂቃዎች ወልዋሎዎች የተሻለ ቢንቀሳቀሱም ጨዋታው ሊጠናቀቅ የተወሰኑ ሰከንዶች ሲቀሩ ኤፍሬም አሻሞ ከቡና ተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ከላካትና ወደ ውጪ ለጥቂት ከወጣችበት ኳስ ውጪ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም፡፡


በዚሁ አጋማሽ የተያው ሌላው ክስተት በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አብዱራህማን ፉሲይኒ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት ሳያጋጥመው በዳዊት ፍቃዱ ዳግም ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡

ጨዋታው በቡና 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ነጥቡን ከመሪው ሀዋሳ ከተማ ጋር ማስተካከል ችሏል።