ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር መካከል ተካሂዶ በባለሜዳዎቹ 2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ አስመልክቶ የክለቦቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።
ስቴዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
” ተጋጣሚያችን ጥሩ ቡድን እንደሆነ እናውቅ ነበር። በመሆኑም ተገቢውን ክብር ሰጥናቸው ነገሮችንም በትክክል ለማስኬድ ሞክረናል። ከግብፁ ክለብ ጋር ሲጫወቱም ስለተመለከትናቸው የቤት ስራችንን በአግባቡ ሰርተን ወጥተናል። ያለፉት ሁለት ጨዋታዎችን ግብ ሳናስቆጥር መውጣታችን አጥቂዎቻችን ከመጎዳታቸው ጋር የተያያዘ ነው። ዛሬ ደግሞ ሳላዲን መመለሱ ብዙ ልዩነት ፈጥሯል። እሱ በሀገሪቱ ካሉ ምርጥ እና ብዙ ልምድ ካላቸው አጥቂዎች ውስጥ አንዱ ነው። እሱን መልሰን ማግኘታችን እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። የመጀመሪያው ዕቅድ ለስልሳ ደቂቃዎች ብቻ ሜዳ ላይ እንዲቆይ ማድረግ ነበር። ነገር ግን ጥሩ ስሜት ስለተሰማው ጨዋታውን እንዲጨርስ አድርገናል። አሁን ደግሞ ለእሁዱ ጨዋታ ዝግጁ እንዲሆን የማገገሚያ ስራዎች ላይ እናተኩራለን።
” በአካል ብቃቱ መውረዳችን ዋነኛው የተበለጥንበት ምክንያት ነበር።” ዩሱፍ ዓሊ (ጅማ አባ ጅፋር ረዳት አሰልጣኝ)
“ከአራት ቀን በፊት የነበረው ጨዋታ በመጠኑ አቅም እንድንጨርስ አድርጎናል። ከእረፍት በፊት ትንሽ እንሻል ነበር። በረጃጅም ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት ወደኛ እየመጡ ነበር ፤ ተከላካዮቻችንን አስቀርተን በመጫወት ተቋቁመናቸው ኳስ መስርተን ለመውጣትም ጥረት እያደረግን ነበር። ከእረፍት በኋላ ግን ተዳክመን ነበር። እነሱ ደግሞ ይበልጥ ተነሳሱ ፤ በተለይም ጎሉን ካስቅጠሩ በኋላ ይበልጥ ተነሳስተዋል። በአካል ብቃቱ መውረዳችን ግን ዋነኛው የተበለጥንበት ምክንያት ነበር።”