በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስሩ ከሚገኙ ክለቦችና ባለ ድርሻ አካላት የሚሳተፉበት በእግርኳሱ ላይ የሚመክር ውይይት መድረክ እንዲሁም በ13ኛ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለተሳተፉ ክለቦች በየደረጃው የገንዘብ ክፍፍል መርሐግብር በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል አዘጋጅቷል።
የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌደሬሽን በስሩ የሚገኙ በሁሉም ሊጎች የሚሳተፉ ክለቦች እና በእግርኳሱ ዙርያ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት በከተማው የእግርኳስ እንቅስቃሴ ዙርያ የሚመክር የውይይት መድረክ እንዲሁም12ኛውን የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ለተሳተፉ ክለቦች በየደረጃው የገንዘብ ክፍፍል ለማድረግ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በታደሙበት የፊታችን ታህሳስ 23 ከ08:00 ጀምሮ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።
08:00 በሚጀምረው በዚህ መርሐግብር የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዓመት አንድ ጊዜ የአዲስ አበባ የሲቲ ካፕ ውድድርን በተሳካ ሁኔታ ከማዘጋጀት በዘለ በስሩ ከሚገኙ ከክለቦች ጋር በተለያዮ ጉዳዮች ዙርያ በመቀራረብ በጋራ አብሮ የመስራት ውስንነት እንዳለበት በማንሳት በተደጋጋሚ ጊዜ ክለቦች የሚያቀርቡበትን ወቀሳ ለማስተካከል በማሰብ በተዘጋጀው በዚህ የምክክር ጉባዔ ፌዴሬሽኑ ብዙ ግብዓቶችን በመውሰድ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራትና ራሱን ለማዘጋጀት ይረዳዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በመቀጠል ሁለተኛው መርሐግብር ስኬታማ ሆኖ በተጠናቀቀው 13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ለተሳታፊ ለሆኑት ስምንቱ ክለቦች ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ 48% የገንዘብ መጠን ለክለቦቹ የሚከፋፈልበት ፕሮግራም ነው። በዚህም መሰረት አንደኛ ለወጣው ኢትዮጵያ ቡና 15%፣ ሁለተኛ ለወጣው ባህር ዳር ከተማ 10%፣ ሶስተኛ ለወጣው ጅማ አባ ጅፋር 7%፣ አራተኛ ለወጣው መከላከያ 4% እንዲሁም ቀሪው በየደረጃቸው 3% ለየክለቦቹ የሚሰጣቸው ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ለአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተለያዮ ዘርፎች መልካም አስተዋፆኦ ላበረከቱ አምስት ግለሰቦች ልዩ የእውቅና ሸልማት መርሐግር እንደሚካሄድ ሰምተናል።