የቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ 2009 ሐምሌ ወር በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውስ ጋር በነበረው የምድብ ጨዋታ በደረሰበት ጉዳት ለስድስት ወራት ከሜዳ ርቆ መጋቢት ላይ በሌላ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዩጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ሲገናኝ በመጨረሻ ደቂቃ በአቡበከር ሳኒ ቀይሮ ቢገባም ብዙም ሳይቆይ የጉልበት ጉዳቱ ዳግም አገርሽቶበት ለተጨማሪ አንድ ዓመት ከሜዳ ርቆ ቆይቷል። በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶም ከረጅም ወራት በኋላ ዳግም በዘንድሮ ዓመት የውድድር ዘመን ወደ ሜዳ ተመልሷል።
ትላንት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን 2-0 በረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ በመጀመርያው አሰላለፍ ላይ የገባው ሳላዲን ለቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎሉን አስቆጥሯል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው ሳላዲን ከረጅም ጉዳት ቆይታ በኋላ ወደ ሜዳ መመለሱ እና ጎል ማስቆጠሩ ደስታ እንደፈጠረለት ተናግሯል። “ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ነው ወደ ሜዳ የተመለስኩት። አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፤ ቡድናችንም ወቅታዊ አቋም ጥሩ አልነበረም። ተደጋጋሚ ነጥቦች እየጣልን ነበር። በዛ ላይ ቀጣይ ጨዋታችን ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነው። ዛሬ በማሸነፋችን እና ጎልም በማስቆጠሬ እጅግ ደስ ብሎኛል።” ብሏል።
በ2009 ከአልጄርያ ተመልሶ ቅዱስ ጊዮርጊስን በድጋሚ ከተቀላቀለ ወዲህ በመጀመርያው ዓመት ጥሩ ጊዜን ቢያሳልፍም ጉዳት ከእግርኳስ አርቆት ቆይቷል። ሳላዲን አስቸጋሪውን ጊዜ ” ባላስታውሰው ደስ ይለኛል።” ሲል ይገልጸዋል። “በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። እግርኳስን ለማቆም አስቤ ሁሉ ነበር። ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን በድጋሚ ለመጫወት ችያለው፤ በጣም ደስተኛ ነኝ። እኔን በትዕግስት ለጠበቀኝ ክለቤ ብዙ አገልግሎት መስጠት እፈልጋለው። ” ሲልም ጨምሮ ገልጿል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ትላንት ጅማ አባ ጅፋርን ያሸነፈ ሲሆን ጥሩ ካልሆነ አጀማመር በኋላ ማሸነፍ መቻላቸው ለቀጣይ ጨዋታዎች መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው የገለፀው ሳላዲን የዚህ ዓመት እቅዳቸው ወደ አፍሪካ ውድድር መመለስ እንደሆነ ተናግሯል።
” ምንግዜም በእግርኳስ ያለፈው ውጤት መድገም ካልቻልክ ጫና እየሆነብህ ይመጣል። አሁን እየተነጋገርን ያለነው ያለፈውን ረስተን ጥሩ ነገር ለማሳየት ጠንክረን መስራት እንዳለብን ነው። አሁል በአካል ብቃት ጥሩ ሁኔታ ላይ ነን። በራስ መተማመን ላይ ነበር የሚያስቸግረን። ዛሬ (የትላንቱ ጨዋታ) በጥሩ ሁኔታ ማሸነፋችን ለቀጣዩ ጥኩ መነሳሳት የሚፈጥር ነው።
” ዋና ዓላማችን የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ወደ አፍሪካ ውድድሮች ዳግም መመለስ ነው። የዘንድሮ የት ስራችን ይሄ ነው። ይህን ለማሳካት ነው አቅደን እየሰራን ያለነው። ”
ሳላዲን ትላንት የአጥቂ መስመር ተጣማሪው ስለሆነው አቤል ያለውም የሚከተለውን ብሏል። ” አቤል በጣም ፈጣን ተጫዋች ነው። እኛ ቡድን ውስጥ እንዲህ ያሉ አጥቂዎች በጣም ያስፈልጋሉ። ወደፊት በጣም የሚያድግ ተጫዋችነው። እዚህ ሀገር ብቻ ሳይሆን በኢንተርናሽናል ደረጃ ወጥቶ መጫወት የሚችል ነው። ጠንክሮ ከሰራ ጥሩ አቅም አለው፤ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይችላል። ”
በመጨረሻም ከወራት በኋላ ያስቆጠራት ጎልን በጉዳቱ ወቅት ባሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ ሀለሉ ከጎኑ ለነበሩት ሁሉ በመታሰብያነት አበርክቷል።