ደደቢት ከፋሲል ከነማ ጋር ላለበት የስምተኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታ ወደ ጎንደር አያመራም።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የትግራይ እና የአማራ ክልል ክለቦች እርስ በርስ የሚገናኙባቸውን ጨዋታዎች በሜዳቸው እንዲያደርጉ የተለያዩ ምክክሮችን ሲያደርግ መሰንበቱ ይታወቃል። ከሳምንት በፊትም የስፖርት ኮምሽን ፣ ፌዴሬሽኑ እና የሁለቱ ክልል ክለቦች ከተነጋገሩ በኋላ ክለቦቹ በየሜዳቸው ጨዋታዎቻቸውን ያካሂዳሉ ቢባልም እስካሁን ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ ጨዋታዎቹ ሲደረጉ እየታየ አይገኝም።
ከነገ ጀምሮ እንደሚከናወኑ ከሚጠበቁ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የፋሲል ከነማ እና ደደቢት ጨዋታም ቀጣዩ ላልተወሰነ ጊዜ የሚተላለፍ ጨዋታ ሆኗል። ፋሲል ከነማ በ16/04/2011 በጻፈው ደብዳቤ ለደደቢቱ ጨዋታ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ቢገልጽም የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ጨዋታውን ለማድረግ ወደ ጎንደር እንደማይጓዝ ታውቋል። የደደቢቱ ቡድን መሪ አቶ ኤፍሬም ለሶከር ኢትዮጵያ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩትም ” እኛ በትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ነው ያለነው። የክልላችን ፌደሬሽንም ጨዋታውን ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም። እኛም ከትግራይ እግር ኳስ ፈደሬሽን ቃል አንወጣም።” ብለዋል።
የሊጉን ተስተካካይ ጨዋታዎች ቁጥር በየሳምንቱ እንዲጨምር ምክንያት የሆነው የሁለቱ ክልል ክለቦች ጉዳይ መፍትሄ አለማግኘት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በዘጠነኛው ሳምንትም ወልዋሎ ዓ.ዩ ከፋሲል ከነማ እንዲገናኙ መርሀ ግብር ወጥቶላቸዋል።