የወልቂጤ ከተማ እግርኳስ ክለብን በአምበልነት እያገለገለ የነበረው መዝገቡ ወልዴ በድንገተኛ ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ታኅሳስ 16 በ1982 ዓ.ም የተወለደው መዝገቡ ወልዴ የእግርኳስ ህይወቱን ከፕሮጀክት አንስቶ ህይወቱ እስከምታልፍ ድረስ ሲመራ የቆየ ሲሆን በደቡብ ክልል ፕሮጀክት ቀጥሎም ወልቂጤ ከተማ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ክለቡን በአምበልነት ለ11 ዓመታት አገልግሏል። በ2007 ለሲዳማ ቡና የመጫወት እድልም አግኝቶ የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ወደ መጀመርያ ክለቡ በድጋሚ ተመልሷል። በዚህ ዓመት ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሎም ነበር።
በክለቡ እና በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በነበረው መልካም ባህርይ አንቱታ ያተረፈው መዝገቡ ከእግርኳሱ በተጨማሪ በትምህርቱ ገፍቶ በ2002 ከመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ድግሪ ማግኘት ችሎ ነበር።
የመዝገቡ ስርዐተ ቀብር ነገ ቅዳሜ ታኅሳስ 20 ቀን 2011 በወልቂጤ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን የሚፈፀም ሲሆን ወልቂጤ ከተማም በተጫዋቹ ሞት የተሰማውኝ ሀዘን ገለጿል። ተጫዋቹ ይለብሰው የነበረው 2 ቁጥር ማልያም ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንዳይለበሱ መወሰኑ ታውቋል።
ሶከር ኢትዮጵያ በተጫዋቹ ህልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሠቦቹ፣ ለቡድን አጋሮቹ፣ ለወዳጆቹ እና ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ትመኛለች፡፡