በመቐለ 70 አንደርታ የነበራቸውን የአንድ ዓመት የውል ጊዜ አጠናቀው በክረምቱ ድሬዳዋ ከተማን ለማሰልጠን የተስማሙት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለእሁዱ የወላይታ ድቻ ጨዋታ ከቡድኑ ጋር አብረው ወደ ሶዶ አልተጓዙም።
ከፍተኛ በጀት በማውጣት በርካታ ተጫዋቾችን ቢያዘዋውርም ያለፉትን ሦስት ዓመታት የውጤት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ላለመውረድ ሲታገል የቆየው ድሬዳዋ ከተማ ከዚህ የውጤት ቀውስ በማውጣት በተሻለ ደረጃ ቡድኑን ከፍ ያደርጉታል በሚል በክረምቱ የዝውውር ወቅት ነበር አሰልጣኝ ዮሃንስ የቀጠሩት። በውድድር ዓመቱን አምስት ጨዋታ ብቻ ያደረጉት አሰልጣኝ ዮሃንስ አሁን እየወጡ እንዳሉት መረጃ ከሆነ ከድሬዳዋ ጋር ሊለያዩ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ይገኛል። ቡድኑ የፊታችን እሁድ ሶዶ ላይ ከወላይታ ድቻ ጋር ላለበት ጨዋታ ከድሬዳዋ በመነሳት ትላንት አዲስ አበባ ሲገባ አሰልጣኝ ዮሃንስም ከቡድኑ ጋር አብረው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ቢሆንም ዛሬ ወደ ሶዶ ካቀናው የቡድኑ ስብስብ ጋር አብረው ያልተጓዙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ 10:00 ላይ በወላይታ ድቻ ሜዳ የመጨረሻ ልምምዱን በሰራበት ወቅት አለመገኘታቸው ከድሬ ጋር ይለያዩ ይሆን የሚለውን ጥርጣሬ አስፍቶታል።
በክለቡ እና በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በኩል ያለውን ሁኔታ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ያልተሳካ ቢሆንም የክለቡ አመራሮች ችግሩ ምን እንደሆነ አጣርተው ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል። ምንም እንኳ ጥረቱ በክለቡ አመራሮች በኩል ይቀጥል እንጂ ሶከር እንዳገኘቸው መረጃ ከሆነ ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከቡድኑ ጋር አብሮ የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ሲሰማ እንደ ምክንያት እየቀረበ ያለው ደግሞ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ የቀረበባቸው ተቃውሞ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ድሬዎች በውድድር ዓመቱ እስካሁን አምስት ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን በሁለት ሽንፈት፣ በሁለት አቻ እና በአንድ ድል በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።