ከስምንተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብሮች መካከል አዳማ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ የሚገናኙበት ጨዋታ የዛሬ የመጀመሪያ የቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን ትኩረት ይሆናል።
አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በ09፡00 በሚጀምረው ጨዋታ ከሽንፈት የተመለሰው አዳማ ከተማ ከድሬዳዋ ነጥብ የተጋራው ደቡብ ፖሊስን ያስተናግዳል። ከአምስት ሳምንታት በኋላ እዛው ሜዳቸው ላይ መቐለን በማሸነፍ የመጀመሪያውን ድል ያጣጣሙት አዳማዎች በሰባተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ተሸንፈዋል። እጅግ ቀዝቃዛ አጀማመር ያደረጉት አዳማዎች አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ብቻ ቢቀራቸውም 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከተጋጣሚያቸው በሁለት ደረጃ ዝቅ ብለው የሚገኙት ደቡብ ፖሊሶችም ሁሉንም ጨዋታ ቢያደርጉም ወደ ላይ ከፍ ማለት አልቻሉም። በርግጥ ቡድኑ ከአራት ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ ነጥብ መጋራት መቻሉ መጠነኛ እፎይታ የሚሰጠው ነው። ነገር ግን ሁለቱ ተጋጣሚዎች ካሉበት ሁኔታ አንፃር ከነገው ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል።
በባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች ቡድን ውስጥ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ምኞት ደበበ ፣ ዐመለ ሚልኪያስ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ሱራፌል ጌታቸው ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን የቡድኑ ወሳኝ አማካይ ከንዓን ማርክነህም በቡናው ጨዋታ ተጎድቶ የወጣ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የጉዳት ዝርዝሩን የተቀላቀለ አምስተኛ ተጫዋች ሆኗል። በደቡብ ፖሊስ በኩል አበባው ቡታቆ ከጉዳት የተመለሰ ሲሆን በድሬዳዋው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጉዳት የገጠመው አማካዩ ኤርሚያስ በላይ እና ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለም ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
አዳማ ከተማ ከነዓንን ማጣቱ በብዙ መልኩ የሚጎዳው መሆኑ እርግጥ ነው። ወደ ግራ ያደላውን የቡድኑን ማጥቃት ከበረከት ደስታ ጋር የሚመራው ከንዓን የሚተውን ክፍተትም ሐብታሙ ሸዋለም እንደሚሞላው ይጠበቃል። የአዲስ ህንፃ ተሳትፎ ተደምሮበትም አዳማ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት በመሞከር ከመስመር ተከላካዮቹ ሁለቱ ሱለይማኖች ተሳትፎ ጋር በበረከት እና ቡልቻ በኩል ወደ ደቡብ ፖሊስ የግብ ክልል ለመድረስ እንደሚጥር ይጠበቃል። ነገር ግን ደቡብ ፖሊስ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ መጫወቱ የሚቀር አይመስልም። ድሬዳዋ ላይ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉባቸው ደቡብ ፖሊሶች ለተከላካይ መስመራቸው በቂ ሽፋን ለመስጠት የአዳማን ጫና ለመቋቋም ከመጣር ባለፈ ከቆሙ ኳሶች እና ከመልሶ ማጥቃት የግብ አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩበት አግባብ ይኖራል። ሆኖም የቡድኑ ተለዋዋጭ የተጫዋቾች አጠቃቀም ለዚህ የጨዋታ ሂደት የሚሆነውን አጥቂ ለማግኘት ያስቸገረውም ይመስላል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተዋል። በውጤቱም ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በአምስቱ ጨዋታዎች ከተቆጠሩት አስር ግቦች ውስጥም አምስቱ የአዳማ አምስቱ ደግሞ የደቡብ ፖሊስ ናቸው።
– አዳማ ላይ በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች ውስጥ የመጀመሪያው በ1-1 ውጤት ሲጠናቀቅ ሁለተኛውን ደቡብ ፖሊስ 1-0 አሸንፏል።
– አዳማ ከተማ ሜዳው ላይ ሦስት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ሽንፈት ፣ አቻ እና ድል ያስመዘገባቸው ውጤቶች ናቸው።
– ደቡብ ፖሊስ በተመሳሳይ ከሜዳው ውጪ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጎ አንድ ነጥብ እና አንድ ጎል አስመዝግቧል።
ዳኛ
– በመጀመሪያው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘውን ጨዋታ እና በስድስተኛው ሳምንት በዝግ የተከናወነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማን ጨዋታ የዳኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ ይህን ጨዋታ ይመራዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-2-3-1)
ሮበርት ኦዶንካራ
ሱሌይማን ሰሚድ – ቴዎድሮስ በቀለ – ተስፋዬ በቀለ – ሱሌይማን መሐመድ
አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ
ቡልቻ ሹራ – ሐብታሙ ሸዋለም – በረከት ደስታ
ዳዋ ሁቴሳ
ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)
ዳዊት አሰፋ
ዘሪሁን አንሼቦ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ
ኄኖክ አየለ – ቢኒያም አድማሱ – ዘላለም ኢሳያስ
መስፍን ኪዳኔ – በኃይሉ ወገኔ – ብሩክ ኤልያስ