ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የሮዱዋ (የወንድማማቾች) ደርቢን እንደሚከትለው እናስዳስሳችኋለን።

የሀዋሳ ባለሰው ሰራሽ ሜዳ ስታድየም እስካሁን ሽንፈት ያላገኘው ሲዳማ ቡና እና በሊጉ አናት የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ በሮዱዋ ደረቢ ነገ 09፡00 ላይ ያገናኛል።ሁሉንም ጨዋታዎች ያከናወኑት ሀዋሳዎች ሰባተኛው ሳምንት ደግሞ በሽረ ላይ ባሳኩት የ6-1 ድል በግብ አንበሽብሿቸው አልፏል። በመሆኑም ተስተካካይ ጨዋታዎች ያላቸው ተከታዮቻቸውን መምራታቸውን ቀጥለዋል። በአንፃሩ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የነበራቸው ጨዋታ የተላለፈው ሲዳማዎች ወደ ሽረ ተጉዘው ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ 14 ቀናት በኋላ ነው ወደ ደርቢው ጨዋታ የሚያመሩት። ሁለቱ ክለቦች አሁን ላይ የሚገኙበት አቋም ጥሩ መሆን ከደርቢው ስሜት ጋር ተዳምሮም የነገውን ጨዋታ ከፍተኛ የፉክክር ስሜት እንደሚያላብሰው ይጠበቃል። 

ሀዋሳ ከተማ የስድስት ጨዋታ ቅጣቱን ካላጠናቀቀው አይሪቮሪኮስታዊው ተከላካይ ያኦ ኦሊቨር ውጭ የጉዳትም ሆነ ቅጣት ዜናዎች የሉበትም። በሲዳማ ቡና በኩልም የቁርጭምጭሚት ጉዳት ከገጠመው አጥቂው መሀመድ ናስር ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው፡፡

መልኩን ለውጦ የመጣው ሀዋሳ ከተማ በቀጥተኛ አጨዋወቱ ገፍቶበታል። ለአቀራረቡ ምቹ የሆነው እስራኤል እሸቱን መዳረሻ ያደረጉ ተሻጋሪ እና ከኋላ መስመር የሚላኩ ኳሶች ነገም ከሀይቆቹ ይጠበቃሉ። የአዳነ ግርማ መመለስም ከጥልቅ አማካይ ቦታ ላይ ለሚሻገሩ ኳሶች ይበልጥ ምቹ ይሆናል። በሽረው ጨዋታ በርካታ የቡድኑ ተሰላፊዎች ወደ ግብ አስቆጣሪነቱ መምጣታቸው ደግሞ የእስራኤልን ኃላፊነት የሚጋሩበት በራስ መተማመን እንደሚጨምርላቸው ይታሰባል። ሲዳማ ቡናዎችም በተመሳሳይ በመስመር አጥቂዎቻቸው ፍጥነት ላይ የተመሰረተ አጨዋወታቸው ይጠበቃል። በተለይም የቡድኑ ዋነኛ ግብ አዳኝ  አዲስ ግደይ ከደስታ ዮሀንስ ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች የደርቢው ድምቀት የመሆን አቅም ይኖራቸዋል። በአጠቃላይ የጨዋታው እንቅስቃሴ ግን የግብ ዕድሎች በተደጋጋሚ የሚታዩበት እና በፉክክር የተሞላ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በሊጉ ለ18 ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች እኩል 5 ጊዜ ተሸናንፈው 8 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ሀዋሳ 19 ጎሎች ሲያስቆጥር ሲዳማ 21 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል።

– ሀዋሳ ላይ በተካሄዱ 9 ጨዋታዎች ሀዋሳ ሁለት ጊዜ ፣ ሲዳማ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። ስድስቱ ቀሪ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።

– ሲዳማ ቡና እስካሁን ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በዛው ልክም ግብ አስተናግዶባቸዋል። የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ አዲስ ግደይም በእያንዳንዱ ጨዋታ ግብ አለው።

– ሀዋሳ ከተማ በአራት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣ ሲሆን ሀዋሳ ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በድል ተወጥቷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የመሀል ዳኝነት ይከናወናል። ቴዎድሮስ እስካሁን በሦስተኛው ሳምንት ስሑል ሽረን ከአዳማ ከተማ እንዲሁም በስድስተኛው ሳምንት ደግሞ ባህር ዳር ከተማን ከኢትዮጵያ ቡና ባገናኙት ጨዋታዎች ላይ ዳኝቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሃ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ በቀለ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ  – ዮሴፍ ዮሀንስ – ወንድሜነህ ዓይናለም

አዲስ ግደይ – ሀብታሙ ገዛኸኝ  – ጫላ ተሺታ

ሀዋሳ ከተማ ( 4-2-3-1) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

አዳነ ግርማ  – መሣይ ጳውሎስ 

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ታፈሰ ሰለሞን – ኄኖክ ድልቢ

እስራኤል እሸቱ