በግዙፉ የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ባህርዳር ከተማ መከላከያን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ቀጣዩ የቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት ነው።
09፡00 ላይ የሚጀምረው የባህር ዳሩ ጨዋታ በሰባተኛው ሳምንት ድል የቀናቸውን ሁለቱን ቡድኖች እርስ በርስ የሚያገናኝ ይሆናል። እስካሁን ሽንፈት ካልገጠማቸው ሁለት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ባህር ዳር ከተማ መልካም አጀማመር አድርጎ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞም በኢትዮጵያ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ላይ ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገብ ችሏል። ሊጉን በድል ቢጀምሩም ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፏቸው በኋላ ተቀዛቅዘው የታዩት መከላከያዎችም ሳምንት ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስተው 3-1 በማሸነፍ ወደ ሊጉ ወገብ ከፍ ማለት ችለዋል። ሁለቱ ቡድኖች ከአሸናፊነት በመምጣታቸው እና ካሏቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች አንፃር ወደ ላይ ከፍ የማለት ዕድል ያላቸው በመሆኑም ጨዋታው ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ባህር ዳር ከተማ ምንም የቅጣት ዜና የሌለበት ሲሆን በጉዳት ምክንያት ግን ሁለት ወሳኝ ተጨዋቾቹን በነገው ጨዋታ ያጣል። ክለቡ በመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎ ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግብ እየረዱ ካሉ ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ወሰኑ አሊ እና ሌላኛው አጥቂ ጃኮ አራፋት በደቡብ ፖሊሱ ጨዋታ በገጠማቸው ጉዳት ለነገ አይደርሱም። በመከላከያ በኩል ቴዎድሮስ ታፈሰ ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ወደ ሜዳ ሲመለስ አማኑኤል ተሾመ ፣ አቅሌሲያስ ግርማ እና አቤል ማሞ ግን ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ወደ ባህር ዳር አልተጓዙም።
እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች የተረጋጋ የመጀመሪያ አሰላለፍ የነበራቸው ባህር ዳሮች ወሰኑን እና አራፋትን በአንዴ ማጣታቸው የፊት መስመራቸውን አስፈሪነት ሊቀንሰው ይችላል። ነገር ግን የተጋጣሚያቸው የመሀል ሜዳ ጥንካሬ በመስመር አጥቂዎቻቸው ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመሰንዘር እንዲመርጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ከዚህ ውጪ ከበስተ ኋላው ክፍተት ሲኖር በሚጣሉ ኳሶች ግቦችን ሲያስተናግድ የሚታየው መከላከያ በባህር ዳር ቀጥተኛ ኳሶችም ጫና ውስጥ ሊገባ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በመሆኑም የጣና ሞገዶቹ የፊት መስመር ተሰላፊዎች የሚፈጥሩት ጫና ወሳኝነት ከፍ ያለ ነው።
በጦሩ በኩል በወላይታ ድቻው ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ የነበረው አይነት እንቅስቃሴን ለመድገም የሚደረግ ጥረት እንደሚኖር ይገመታል። በዚህም ቡድኑ በሚመርጠው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ለጠንካራው የባህር ዳር የተከላካይ መስመር የተጠጋ እና በመሀላቸው የሚኖረውን ክፍተት ለመጠቀም የሚያስችል የአጥቂዎች ቦታ አያያዝ እንዲሁም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ራሳቸውን ነፃ አድርገው ኳስ የሚቀበሉ አማካዮች ባህሪን የተላበሰ ቡድን ይጠበቃል። በተጨማሪም የቴዎድሮስ ታፈሰ መመለስ ደግሞ ቡድኑ ከቀጥተኛ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚያስችለውም ይታመናል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪይ የፕሪምየር ሊግ የርስ በርስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
– ከአዲስ ግደይ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ውጪ እስካሁን ከክፍት ጨዋታ ምንም ግብ ያልተቆጠረበት ባህር ዳር ከተማ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ከሜዳ ወጥቷል።
– ባህር ዳር ከተማ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን በሜዳው ያደረገ ሲሆን አራት ነጥቦችንም ማሳካት ችሏል። መከላከያም በተመሳሳይ ከሜዳው ውጪ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ነጥቦችን አሳክቷል
– ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስቆጠሩት መከላከያዎች እስካሁን ግብ ሳያስተናግዱ የወጡበት ጨዋታ የለም።
ዳኛ
– በአራተኛው ሳምንት ወልዋሎ እና ደቡብ ፖሊስን ያገናኘውን ጨዋታ በመምራት ስድስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ያስመለከተው አዳነ ወርቁ ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህርዳር ከተማ (4-3-3)
ምንተስኖት አሎ
ሣህለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ
ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ
እንዳለ ደባልቄ – ፍቃዱ ወርቁ –ግርማ ዲሳሳ
መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)
ይድነቃቸው ኪዳኔ
ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ
ቴዎድሮስ ታፈሰ
ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ
ተመስገን ገብረኪዳን
ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ