‹‹ ለውጤቱ መመስገን ያለባቸው ተጫዋቾቼ ናቸው ›› አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቡሩንዲን አሸንፎ ለ2016 የቻን ውድድር አልፏል፡፡ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየትም ለድላቸው ተጫዋቾቻቸውን አመስግነዋል፡፡

‹‹ ነባር ተጫዋቾች አዲሶቹን እያበረታቱ ብሄራዊ ቡድኑን እንዲላመዱ እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የብሄራዊ ቡድን ማልያ የለበሱት አሊ ረዲ እና ፋሲል ተካልኝ በወጣት ቡድን በነበሩበት ጊዜ ከግብፅ ጋር ስላደረጉት ጨዋታ እንደምሳሌ ወስደው ውጤቱን መቀልበስ እንደሚችሉ ተነጋግውበታል፡፡ (የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ለአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ለማለፍ ከግብፅ ጋር ባደረገው ጨዋታ 5-0 ተሸንፎ ከካይሮ ቢመለስም በመልሱ አዲስ አበባ ላይ በተመሳሳይ 5-0 አሸንፎ ነበር) 90 ደቂቃ በሚገባ ተጫውተን ግቦች ማስቆጠር እንዳለብንና ብዙ ነገር ማድረግ እንደምንችል ተነጋግረን በር ወደ ሜዳ የገባነው፡፡

‹‹ ስለ ደጋፊዎቹ ምንም ልል አልችልም፡፡ ማውራት የምችለው ስለተጫዋቾቼ ነው፡፡ ተጫዋቾቼ የሀገር አደራ ስላለባቸውና ያላቸውን ሁሉ መስጠት እዳለባቸው ስላመኑ ሜዳ ላይ የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ ለውጤቱ መመስገን ያለባቸው ተጫዋቾቼ ናቸው፡፡ ››

ስለ መሃመድ ናስር ቅያሪ

‹‹ መሃመድ ናስርን በእረፍት ሰአት የቀየርንበት ምክንያት በቅርቡ ቡድናችንን በመቀላቀሉና ቶሎ ወደ ሲስተም ውስጥ ባለመግባቱ ነው፡፡ መሃመድ ከአማካዮቹ ጋር መግባበት ስላልቻለና በጨዋታው እምብዛም ስላልተሳተፈ ቡድናችን ደግሞ ግብ ማግባት ስላለበት ነው የቀየርነው፡፡ ››

የቡድኑ ለቻን ማለፍ…

‹‹ ለቻን ማለፋችን ለውጡ ለተጫዋቾች ነው፡፡ ውጤት ሲጠፋ የሚከተለውን አሉታዊ ነገርን መቀልበስ ይቻላል፡፡ ስራ ላይ ካተኮርን ወሬ በስራ ይደመሰሳል፡፡

‹‹ ለቻን ማለፍን እንደ ስኬት እቆጥረዋለው፡፡ የሰራነውንም አሳክተናል፡፡ ጫና መቋቋምን እየለመድን መጥተናል፡፡ ከሳኦቶሜ ጋር ረጅም ጉዞ በማድረጋችን እና በፊፋ ደረጃ ደካማ በሆነች ሃገር በመሸነፋችን ጫና ውስጥ በመግባታችን በመልሱ ጨዋታ ለማሸነፍ በፍጥነት በማጥቃት መጫወት ነበረበን፡፡ አሁን ግን ተጫዋቾቼ እየበሰሉ ነው፡፡ እኔን ጨምሮ ፋሲል እና አሊ ረዲ በብሄራዊ ቡድን በማሳለፋቸው ልምዳቸውን ለተጫዋቾች በማካፈል ብስለት እንዲያገኙ እየረዱ ነው፡፡ ››

ስለ ኤልያስ እና ጋቶች

‹‹ ጋቶች እኛ ያልነውን ነው ያደረገው፡፡ ኤልያስ ደግሞ ነፃ ሆኖ እንዲጫወት ነው ያደረግነው፡፡ በተቻለ መጠን ወደ ፊት እንዲሄድ ነው የፈለግነው፡፡ በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ልምድ በማካበቱ የተነገረውን ሃላፊነት ተወጥቷል፡፡ ››

ያጋሩ