አዳማ ከተማ ደቡብ ፖሊስን ያስተናገደበት የስምንተኛ ሳምንት መርሐ ግብር በዳዋ ሁቴሳ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በሰባተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 1-0 የተረቱት አዳማ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ ቴዎድሮስ በቀለ እና ሱሌይማን ሰሚድን በምኞት ደበበ እና ሱራፌል ዳንኤል ሲቀይሩ ጉዳት በገጠመው ከነዓን ማርክነህ ምትክ ደግሞ ሙሉቀን ታሪኩ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መጥቷል። በሳምንቱ አጋማሽ በተስተካካይ ጨዋታ ከድሬዳዋ ነጥብ የተጋሩት ደቡብ ፖሊሶች ደግሞ አምስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም መሰረት ኤርሚያስ በላይ ፣ ብሩክ አየለ ፣ ኄኖክ አየለ ፣ ልዑል ኃይሌ እና በረከት ይስሀቅ በአበባው ቡታቆ ፣ መስፍን ኪዳኔ ፣ ብሩክ ኤልያስ ፣ አዲስዓለም ደበበ እና በኃይሉ ወገኔ ተተክተዋል።
ፈጣን አጀማመር በታየበት ጨዋታ እንግዶቹ ደቡብ ፖሊሶች ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይዘው የገቡ ቢመስልም በአመመዛኞቹ ደቂቃዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው ታይተዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሁቴሳ በግምት ከ20 ሜትር ርቀት ላይ በቀጥታ መትቶ ዳዊት ማሞ ባዳነበት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች የከነዓንን አለመኖር ተከትሎ ከፊት ሁለት አጥቂዎችን ተጠቅመዋል። አዳማዎች የመስመር ተከላካዮቻቸውን ባሳተፈ ሁኔታ ወደ ደቡብ ፖሊስ ሜዳ አድልተው የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ሲያጠቁ ቆይተዋል። ነገር ግን የመጀመሪያው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ የተደረገው በደቡብ ፖሊሶች በኩል ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግራ ካደላ የርቀት ቅጣት ምት አበባው ቡታኮ በቀጥታ አሻምቶ ዘሪሁን አንሼቦ በግንባሩ ቢገጭም ሮበርት በአስደናቂ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።
አዳማዎች አደገኛ ሆነው ይታዩ ከነበሩበት የግራ መስመር በ15ኛው ደቂቃ ቡልቻ ሹራ በረከት ደስታን ከግብ ጠባቂ ጋር ያገናኘች ኳስ አቀብሎት በረከት ቢሞክርም ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በዚሁ አቅጣጫ በረከት ወደ ውስጥ ይጥላቸው የነበሩ ኳሶችም በደቡብ ፖሊስ ሳጥን ውስጥ ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ነበር። የመስመር አጥቂዎቻቸውን ጭምር ወደ ኋላ ስበው ለበኃይሉ ተገኔ ቀጥተኛ ኳሶችን ለድማረስ ሲሞክሩ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች ተጋጣሚያቸው በተለይም መሀል ለመሀል የሚሰነራቸውን ጥቃቶች በመመከቱ ተሳክቶላቸው ነበር። ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ ጫና ሲፈጥር ይታይ የነበረውም ከአበባው ቡታቆ ቅጣት ምቶች ነበር። በ39ኛው እና 40ኛው ደቂቃ ላይ ሁለቱ አማካዮች ዘላለም ኢሳያስ እና አዲስዓለም ደበበ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ከባድ የሚባሉ አልነበሩም። በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉቀን ታሪኩን በጥልቀት ወደ ኋላ በመመለስ ክፍተቶችን መፈለጋቸውን የቀጠሉት አዳማዎች የደቡብ ፖሊሶችን ጠንካራ መከላከል ሳይሰብሩ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ጉሽሚያ የበዛበት ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ደቡብ ፖሊሶች እንደመጀመሪያው ሁሉ የማጥቃት ምልክት አሳይተዋል። ሆኖም ይህኛው የተወሰነ ቀጣይነት የታየበት ነበር። የመስመር አጥቂዎቻቸውም ወደ ፊት ገፍተው የታዩባቸው አገጣሚዎች በርከት ብለዋል። ነገር ግን የመጨረሻ የግብ ዕድል የመፍጠር ችግራቸው እስከመጨረሻው የቀጠለ ነበር። በ51ኛው ቡልቻ ሹራ በ56ኛው ደግሞ ዳዋ ሁቴሳ ከቅጣት ምቶች ባደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አጋማሹን የጀመሩት አዳማዎች በበኩላቸው አጥቅተው መጫወታቸውን ገፍተውበታል። ሆኖም ቡድኑ መሀል ለመል ተጋጣሚውን ሰብሮ መግባት ሲከብደው እና ሁለቱን መስመሮች አብዝቶ ለመጠቀም ሲገደድ ተስተውሏል።
በግራ እና በቀኝ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ያሰቡ የሚመስሉት ደቡብ ፖሊሶች 57ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። መስፍን ኩዳኔ በቀኝ መስመር ገብቶ የሞከረው ኳስ ግን በሮበርት ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል። ደቡብ ፖሊሶች ሌላ ተመሳሳይ ዕድል ከማግኘታቸው በፊትም የአዳማ የቀኝ መስመር እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቷል። ቡድኑ በቦታው በሰነዘረው ጥቃት የመስመር ተከላካዩ ሱራፌል ዳንኤል በደቡብ ፖሊስ ሳጥን ውስጥ በዘሪሁን አንሼቦ ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ በመምታት የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረችውን ግብ አስቆጥሯል።
በተቀሩት ደቂቃዎች ደቡብ ፖሊሶች የመስመር አጥቂዎቻቸውን በመቀየር የተሻ ግዛው እና ኄኖክ አየለን አስገብተው በአዲስ ጉልበት አቻ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ነገር ግን በጭማሪ ደቂቃ ቡድኑ ወሳኟን ጎል ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። በግራ መስመር አበባው ቡታቆ ከቆመ ኳስ ሲያሻማ በኃይሉ ወገኔ በጥሩ ሁኔታ ግንባሩ የገጨ ሲሆን ኳስ እና መረብ እንዳይገናኙ ያደረገው የግቡ አግዳሚ ነበር። ጨዋታውን አቀዝቅዘው ኳስ በመያዝ ለመጨረስ ያደረጉት ጥርት የተሳካላቸው አዳማዎችም የዓመቱን ሁለተኛ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል።