የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ አምሰተኛ ሳምንት መርሐ ግብር መካከል አምስቱ ጨዋታዎች እሁድ ተከናውነው ዲላ ከተማ፣ መድን እና አዲስ አበባ ከተማ አሸንፈዋል። ወደ ነገሌ አርሲ ያመራው ሀላባ ደግሞ አስደንጋጭ ሽንፈት ገጥሞታል።
ዲላ ላይ ዲላ ከተማ በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ክለቦች አንዱ የሆነው ሀምበሪቾ ዱራሜን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። በ46ኛው ደቂቃ ላይ ታዲዮስ አንበሴ ለዲላ ከተማ ብቸኛዋን የድል ጎል ማስቆጠር ችሏል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የዲላ ከተማ ግብ ጠባቂ ኳስ ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት ግንባሩ ላይ ጉዳት በመድረሱ ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር። ሽንፈት የገጠመው ሀምበሪቾ ከነበረበት ደረጃ አንድ ዝቅ በማለት በሶስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።
መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጽያ መድን ወላይታ ሶዶን አስተናግዶ ከእረፍት በኋላ በተገኘች ግብ አሸንፏል። ለመድን በ72ኛ ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ምስጋናው ወልደዮሐንስ ነው። ኢትዮጽያ መድን ማሸነፉን ተከትሎ በአምስት ጨዋታ አራቱን አሸንፎ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል።
ፌደራል ፖሊስ ሜዳ ላይ የካ ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአዲስ አበባ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ9ኛው ደቂቃ ላይ አድማሱ አሻግሬ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን የቻሉት አዲስ አበባዎች በ82ኛው ደቂቃ ኢብሳ በፍቃዱ ተጨማሪ ግብ አክሎ 2-0 አሸንፈዋል። በጨዋታው በአዲስ አበባ በኩል አብርሀም ሰኒ በሁለት ማስጠንቀቂያ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ነገሌ አርሲ ሀላባ ከተማን አስተናግዶ ባልተጠበቀ ውጤት 4-1 አሸንፏል። በ19ኛው ደቂቃ ሙባረክ ጀማል በፍፁም ቅጣት ምት ቀዳሚውን ግብ ሲያስቆጥር በ33ኛው ደቂቃ አብዱሀሰን ጀማል እንዲሁም የመጀመሪያው የጨዋታው ክፍል ጊዜ መጠናቀቂያ ላይ ምትኩ ጌታቸው አስቆጥረው የመጀመርያው አጋማሽ 3-0 ተጠናቀቀው። በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ምትኩ ጌታቸው በፍፁም ቅጣት ምት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ ማስቆጠር ሲችል ሀላባን ከሽንፈት ያላደናነች ግብ አብዱላዚዝ ዑመር በ84ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።
በድሬዳዋ ደርቢ ድሬዳዋ ፖሊስ ከናሽናል ሴሜንት አንድ አቻ ተለያይተዋል። ድሬዳዋ ፖሊስ ቀድሞ ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን ቢችልም በ78ኛው ደቂቃ ሄኖክ ፍቃዱ ናሽናል ሲሚንትን አቻ አድርጓል።
የምድብ መሪነቱን ለመድን ያስረከበው ኢኮስኮ ከወልቂጤ የሚያርጉት ጨዋታ የወልቂጤ አምበል የነበረው መዝገቡ ህልፈት ምክንያት ወደ ሰኞ ተሸጋግሯል።