ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ አምሰተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አራቱ እሁድ ዕለት ተከናውነው ሀዲያ ሆሳዕና፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ጅማ አባቡና ማሸነፍ ችለዋል።
ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ 1-2 ሻሸመኔ ከተማ
በዮናታን ሙሉጌታ
የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ዛሬ በመጀመርያ የውድድር ዘመን ጨዋታው ሻሸመኔ ከተማን ባስተናገደበት ፤ ከተቃደለት ሰዓት አርባ ደቂቃ ያህል ዘግይቶ 04:40 ላይ በጀመረው ጨዋታ 2-1 ተሸንፏል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጥሩ ፉክክር የታየበት እና ግቦችም የተስተናገዱበት ነበር። ገና በአንደኛው ደቂቃም ከባድ ሙከራ ሊታይበትም ችሏል። በሙከራው የአውቶሞቲቩ ሚሊዮን ብሬ በረጅሙ ካሳለፈለት ኳስ የፊት አጥቂው ሲሳይ አማረ ሳጥን ውስጥ መግባት ቢችልም የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ቀድሞ ደርሶ አድኖበታል። ይህ ሲሆን ሲሳይ ባንጫ ጉዳት አስተናግዶ ጨዋታው ከጅምሩ ለበርካታ ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል። ከዚህ በኋላ በነበረው አብዛኛው ደቂቃ ሻሸመኔዎች ወደ ፊት ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን በሙከራ ረገድ ግን እምብዛም አልነበሩም። 15ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ቅጣት ምት የአውቶሞቲቭ ሳጥን ውስጥ ሙሉቀን ተሾመ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ሙከራው ወደ ላይ የተነሳበት አጋጣሚ የቡድኑ የተሻለ የግብ ዕድል ነበር።
በተጋጣሚያቸው ጫና በራሳቸው አጋማሽ ለመቆየት የተገደዱት አውቶሞቲቮች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይተሻለ አስፈሪነት ነበረው። በተለይም 33ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት ጫና የግራ መስመር ተከላካዩ ታሪኩ እሸቴ ከሳጥን ውጪ የሞከራት ኳስ ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውበታል። በዚህ መልኩ ሊጠናቀቅ ተቃርቦ የነበረው አጋማሹ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግቦችን አስተናግዷል። በ40ኛው ደቂቃ የሻሸመኔው ዘመን አሸብር በግምት ከ 20 ሜትር ርቀት ላይ ቡድኑ ያገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ሲያስቆጥር ግብ አስተናግደው ከመሀል የጀመሩት አውቶሞቲቮች አጥቂያቸው ወንድምአገኝ አብሬ ከቀኝ በከል ከደረሰው ኳስ ከሳጥን ውስጥ ባስቆጠራት ግብ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ውስጥ አቻ መሆን ችለዋል። ወንድማገኝ በድጋሜ ከቀኝ መስመር የተሻማ ሌላ ኳስም በግንባሩ ገጭቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ አውቶሞቲቮች የተሻለ መነቃቃት ታይቶባቸው ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። ነገር ግን ከአንድ የረጅም ርቀት ሙከራ ውጪ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልሆነላቸውም። ይልቀኑም 55ኛው ደቂቃ ላይ የሻሸመኔው ሙሉቀን ተሾመ ከግራ መስመር ወደ ግብ የላከው ኳስ መረብ ላይ ለማረፍ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ወርቅነህ ዲባባ ለጥቂት ነበር ያዳነው። በአበባየው ስጦታው ጥሩ የመሀል ሜዳ ብቃት ታግዘው አልፎ አልፎ ወደ ግብ ይደርሱ የነበሩት ሻሸመኔዎች ቀጣይ ጥቃታቸው ወደ ግብነት ተቀይሯል። ግቡ 64ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ በረጅሙ የጣለውን ኳስ የፊት አጥቂዎቹ በፈጠሩት ጫና የአውቶሞቲቩ የመሀል ተከላካይ ይደነቁ የሺጥላ ጨርርፎት በራሱ ግብ ላይ ያስቆጠረው ነበር።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ወደ ኋላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያደረጉት ወልቂጤዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ አብርሀም አለሙ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ከቀረው የመልሶ ማጥቃት ሙከራ ውጪ ወደ አውቶሞቲቭ የግብ ክልል በብዛት አልደረሱም። በአንፃሩ አውቶሞቲቮች ፀጋ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ወደ ላይ ከተነሳበት ኳስ በተጨማሪ 78ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪው ወንድምአገኝ አብሬ ከግራ መስመር ከተሻገረ ኳስ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ሲሳይ ፈጥኖ በመውጣት ያከሸፈበትን አጋጥሚ ፈጥረዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባላቸው ኃይል ሙሉ ለማጥቃት የሞከሩት ባለሜዳዎቹ ከመሀመድ ሁሴን የቅጣት ምት በተጨማሪ በመጨረሻ ሰዓት ይደነቁ የሺጥላ ከሲሳይ ጋር ተገናኝቶ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ የሳታትን ኳስ ጨምሮ ሌሎች ሙከራዎችን ቢያደርጉም የአቸነቷን ግብ ሳያገኙ 2-1 ለመሸነፍ ተገደዋል።
አርባምንጭ ከተማ 3-0 ቤንች ማጂ ቡና
በፋሪስ ንጉሴ
አርባምንጭ ላይ በተካሄደው ጨዋታ የአርባምንጭ ሜዳ ከእለት ወደ እለት በተመልካቾች መሞላቱን የቀጠለ ሲሆን ወደ አናት የተጠጋበትን ድል ማስመዝገብ ችሏል። በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት አርባምንጭ ከተማዎች ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት በሚያስችል ሁኔታ አብዛኛውን የመሀልና የመስመር ተጫዋቾቻቸውን ወደተጋጣሚው የግብ ክልል ተጭነው እንዲጫወቱ የተሰጣቸው ትዕዛዝ ለመተግበር እየሞከሩ ሲንቀሳቀሱ ውለዋል።
በ 4-5-1 አሰላለፍ ውጤት አስጠብቀው ለመግባት በሚመስል አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት እንግዳው ቡድንም ጨዋታውን አስቀድመው በማዝግየትና ጨዋታን በተገኘው አጋጣሚ አሸንፈው ለመውጣት ሲሞክሩ ታይተዋል። በጨዋታው የመጀመርያ 10 ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች በራሳቸው ሜዳ ላይ ተመሳሳይ ስህተቶችን ሲሰሩ የነበረ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ታይተዋል። 9ኛው ደቂቃ ላይ አንድነት በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ አለልኝ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት፣ 17ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ ያቀበለውን ኳስ ስንታየሁ በአክሮባት መትቶ ለጥቂት የወጣበት እንዲሁም በ35፣ በ40 እና በ45ኛው ደቂቃ ላይ በስንታየሁ መንግስቱ፣ በአሸነናፊ ተገኝና በአለልኝ አዘነ አማካኝነት በአርባምንጭ በኩል የተደረጉት ሙከራዎች ሲሆኑ ወንድማገኝ ኪራ ያደረገው ጥኩ ሙከራም በቤንች ማጂ በኩል የሚጠቀሱ ናቸው ።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበትና የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን በሜዳው አይበገሬነቱን ማሳየት የቻለበት ነበር። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የአርባምንጭ ከተማው ቴዲ ታደሰ በሁለተኛው አጋማሽ ከመሀል ሜዳ በግሩም እንቅስቃሴ የራሱን የግል ችሎታ ተጠቅሞ አርባምንጮችን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ ለማጥቃት ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ቤንች ማጂዎች የአርባምንጭ ከተማን የተከላካይ ክፍል ለማለፍ ተቸግረዋል። የአርባምንጨ ከተማ የመሀል ክፍል ከፍተኛ የማጥቃት አቅም የፈጠረ ሲሆን በ56ኛው ደቂቃ ስንታየሁ ለፍቃዱ አቀብሎ ፍቃዱ ጥሩ የአጨራረስ አቅሙን ተጠቅሞ ለአርባምንጭ ከተማ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራል። በጨዋታው በተደጋጋሚ ጥፋቶችን በመስራት በሁለት ቢጫ የቤንች ማጂው መስፍን ጎሳዬ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ጨዋታውንም አርባምንጮች አቅልለው እንዲጫወቱ ረድቷቸዋል። 67ኛው ደቂቃ ላይም አለልኝ አዘነ ሁለት ተጫዋቾችን አታሎ 3ኛው ጎል አስቆጥራል። በ90ኛው ደቂቃ ላይ ቤንች ማጂዎችን ከባዶ የምታድናቸውን እድል አግኝተው ያሬድ አማረ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም በባለሜዳው አርባምንጭ ከተማ 3 ለ 0 ተጠናቋል።
ጅማ አባ ቡና 3-2 ስልጤ ወራቤ
በቴዎድሮስ ታደሰ
በሳምንቱ ከተደረጉት የምድቡ ጨዋታዎች ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው ጅማ አባቡና ስልጤ ወራቤን ያገናኘው ጨዋታ እንግዶቹ 2-0 መምራት ቢችሉም በባለሜዳዎቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዘጠና ደቂቃው የጨዋታ እቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተጋጣሚያቸው ላይ መውሰድ የቻሉት ወራቤዎች እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ ጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ረገድ ውስን ነበሩ ። በባለሜዳዎቹ በኩል በመሀል ሜዳ ላይ ከተወሰደባቸው ብልጫ ምክንያት የተሳኩ የኳስ ቅብብሎችን እኳን ማድረግ ሲቸገሩ ተመልክተናል። በ5ኛው ደቂቃ ዳንኤል ራመቶ ከግራ መስመር ያሻገረው ኳስ ካርሎስ ዳምጠው በግባሩ ሞክሮ በሽር ደሊል ያዳነበት እንዲሁም ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት ሮቤል አስራት ሞክሮት በድጋሚ በሽር ደሊል በቀላሉ ያዳነበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።
ወራቤዎች በሁለቱም በመስመሮች በኩል የሚያደርጓቸው እቅስቃሴዎች አደገኛ ነበሩ። በ28ኛው ደቂቃ የተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ከድር ታረቀኝ ወራቤን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ወራቤዎች በከድር ታረቀኝ እንዲሁም በተመስገን ዳባ በተደጋጋሚ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ጎል መስቆጠር ሳይችሉ ወደ መልበሻ ቤት አቅንተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ አባቡናዎች መሀል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ክፍተት ከተከላካዮች በሚጣሉ ረጅም ኳሶች ወደፊት በመጣል የአጨዋወታቸውን ቀይረው በመግባት ከመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ጎል ለመቅረብ ቢሞክሩም በእለቱ ጥሩ ሲቀሰቀስ የነበረው ተመስገን ዱባ ሶስት የአባቡና ተከላካዮችን አታሎ ወራቤን መሪነት ወደ 2-0 ቢያሸጋግርም ወራቤዎች ከጅማ አባቡና ደጋፊዎችች የድጋፍ ጫና መቋቋም ተስኗቸው በእጃቸው ያስገቡትን ሶስት ነጥብ አሳልፈው መስጠት ተገድለዋል።
በ66ኛው ጀቂቃ ተቀይሮ የገባው ሳፎ ቁሪ የወራቤን መሪነት ወደ 1-2 ያጠበበች ግብ ሲያስቆጥር የአቻነቷን ግብ በሳሙኤል አሸበር በ82ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ካርሎስ ዳምጠው ደግሞ በ85ኛው ደቂቃ የአሸናፊነት ግብ በማስቆጠር ከመመራት ወደ አሸናፊነት መሸጋገር ችለዋል። በጨዋታው ላይ የእለቱ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ጨዋታውን ተቆጣጥረው የወጡበት መንገድ ሊያስመሰግናቸው ይገባል ፡፡
ሀዲያ ሆሳዕና 2-1 ነጌሌ ቦረና
ሆሳዕና ላይ ሀድያ ሆሳዕና ነጌሌ በቦረናን አስተናግዶ ከመመራት በመነሳት 2-1 አሸንፏል። በ32ኛው ደቂቃ ለነገሌ ቦረና ፍፁም ታደሰ ግብ አስቆጥሮ ለረጅም ያህል ደቂቃ መምራት ቢችሉም ኢዩኤል ሳሙኤል በ74ኛው እና በ75ኛው ደቂቃ አከታትሉ ባስቆጠራቸው ጎሎች ሆሳዕና ድል አስመዝግቧል።
ነቀምት ከተማ ከ ካፋ ቡና እንዲሁም ካምባታ ሺንሺቾ ከ ቡታጅራ ከተማ ሊያደረረጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረዋል።