ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ከስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ውስጥ ዛሬ በብቸኝነት ጅማ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል። 

ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተስተካካይ ጨዋታች ሽንፈት የገጠማቸው ጅማ አባ ጅፋር እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ዛሬ ጅማ ላይ በ09፡00 ሰዓት እርስ በርስ ይገናኛሉ። የውድድር ዓመቱ ከጀመረ በፕሪምየር ሊጉ እና በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ሜዳቸው ላይ የመጫወት ዕድል ያልነበራቸው ቻምፒዮኖቹ ዛሬ ወደ ጅማ ይመለሳሉ። በሊጉ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ያሳኩት ጅማዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ የ16 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዟቸውን የገታ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ቡና የተሸነፉት ወልዋሎዎች ከዚያ እስቀድሞ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አሁን 6ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ ያስቻሏቸውን አስር ነጥቦች አሳክተው ነበር። በመሆኑም የዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚፋለሙበት ይሆናል።

ጅማ አባ ጅፋር ረጅም ጊዜ ገዳት ላይ ከሚገኘው ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ በተጨማሪ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዐወት ገብረሚካኤልን በጉዳት የማይጠቀም ሲሆን ዳንኤል አድሓኖም ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ በወልዋሎ በኩል በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው። 

ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አቀራረብ ይዘው እንደሚገቡ የሚጠበቁት ጅማ አባ ጅፋሮች ከአማካይ ክፍሉ በተለይም ከመስዑድ መሀመድ ወደ ሦስቱ አጥቂዎች የሚላኩ ኳሶች ዋነኛ የማጥቃት አማራጬቻቸው እንደሚሆኑ ይገመታል። በተለይም ዲዲዬ ለብሪ የሚሰለፍበት የቡድኑ የግራ ወገን ተመራጩ የጥቃት መስመር የመሆን ዕድሉ የሰፋ ሲሆን አይቮሪኮስታዊው አጥቂም ከብርሀኑ ቦጋለ ጋር የሚገናኝባቸው ቅፅበቶች ወሳኝነታቸው የጎላ ነው። የመስመር አጥቂዎቻቸው አጥብበው ወደ ውስጥ በሚገቡባቸው ወቅቶች የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የሚታዩት ጅማዎች የመስመር ተከላካዮቻቸውን ወደ ፊት ገፍተው ማጫወት አጥቂዎቹ የሚተውቱን ክፍተት ከመጠቀም ባለፈ መሀል ላይ ሊገጥማቸው ከሚችለው የቁጥር ብልጫም አንፃር ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ይታመናል።

ከሜዳቸው ውጪ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ ያላቸው ወልዋሎዎች በመስመር አጥቂነት የሚጠቀሟቸውን ተጨዋቾች ወደ ኋላ በመሳብ መሀል ክፍል ላይ ተበራክተው ለዚህኛው ጨዋታ እንደሚደርሱ ይታመናል። ብቸኛው አጥቂያቸው ሪችሞን አዶንጎም ከተከላካይ መስመር ጀርባ የሚኖረውን ቦታ እንዱጠቀም የሚላኩለት ቀጥተኛ ኳሶች ዛሬ በወልዋሎ በኩል የሚጠበቁ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም ግን ቡድኑ መሀል ላይ የሚያቋርጣቸውን ኳሶች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ኋላ የመመለስ ኃላፊነት በሚሰጣቸው በግራ እና ቀኝ ያሉ የማጥቃት አማካዮቹ በኩል ይዞ ወደ ጅማ የግብ ክልል የመግባት ዕቅድም ሊኖረው ይችላል። ይህ እንዲሆን ግን ቡድኑ በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች ላይ የሚታይበትን የቅብብል እና የውሳኔ ስህተቶች ማሻሻል ይገባዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወልዋሎ ሊጉን በተቀላቀለበት የ2010 የውድድር ዓመት ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር 3-0 ሲያሸንፍ የዓዲግራቱ ጨዋታ ደግሞ 1-1 የተጠናቀቀ ነበር።

– ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ግብ አላስተናገደም።

– ወልዋሎ እስካሁን ከመቐለ ወጥቶ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች መካከል አንዱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ተረቷል።

– ወልዋሎ እስካሁን ያሸነፋቸው ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።

ዳኛ

– ዘንድሮ መቐለ እና አዳማ ላይ ሁለት ጨዋታዎችን የዳኘው  ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ዛሬ ደግሞ የጅማውን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)                       

ዳንኤል አጄዬ

ያሬድ ዘውድነህ – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ኄኖክ ገምቴሳ – ይሁን እንዳሻው – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – ቢስማርክ አፒያ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-2-3-1)

አብዱልዓዚዝ ኬይታ

እንየው ካሳሁን –  ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ

ብርሀኑ አሻሞ – አስራት መገርሳ  

አብዱርሀማን ፉሴይኒ –አፈወርቅ ኃይሉ  – ኤፍሬም አሻሞ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ