ፌዴሬሽኑ ራሱን የቻለ የሊግ አስተዳደር የማወቀር ስራን በቅርቡ ሊጀምር ነው

“ክለቦች ራሳቸው የሚመሩት የሊግ ኮሚቴ እንዲቋቋም በእኛ በኩል ቆርጠን ገብተናል። ክለቦች በሞግዚት መመራት የለባቸውም፤ ለእግርኳሱም እድገት ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። ” የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም

ክለቦች ራሳቸው ባቋቋሙት የሊግ አስተዳደር መመራት አለባቸው በሚል ባለፉት ዓመታት የክለቦች ሊግ ለማዋቀር ቢታሰብም በክለቦች መካከል መተማመን ጠፍቶ በተደጋጋሚ  ሀሳቡ ሳይሳካ መቅረቱ ይታወቃል። በ2010 አዲስ የተሾሙት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ክለቦች የራሳቸውን ውድድሮች ራሳቸው መምራት አለባቸው የሚል አቋም በመውሰድ የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዕጣ የማውጣት ፕሮግራም ላይ አደረጃጀቱን እንዲያስፈፅሙ አቶ ሰላሙ በቀለ፤ አቶ አስጨናቂ ለማ እና አቶ ሸረፋ ዴሌቾ መመረጣቸው ይታወሳል። ለወራት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየው ኮሚቴው በቅርቡ ተጨባጭ በሆነ መልኩ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሆነ ም/ፕሬዝደንት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም የኢትዮጵያ ቡና ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ ተናግረዋል።

” የሊጉ ባለቤት ራሳቸው ክለቦች ሊጉን ሊመሩ ይገባል። ሌላ ሞጉዚት አካል መኖር የለበትም። ኮሚቴ ብሎ ዘመናዊ እግርኳስን መጠበቅ አይቻልም። በትርፍ ጊዜ በሰዎች ፍላጎት ላይ ተገድቦ ሚሰራ ስራ አያዋጣም። ሊጉ ውድድሮችን ከመምራት ባለፈ የተሻሉ ትልልቅ ሀሳቦች የሚተገበሩበት ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚስብ ውድድር መሆን አለብን። በእኛ በኩል ሊጉ በክለቦች እንዲመራ ፅኑ አቋም አለን። ለዚህ የሚሆን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች አጠናቀናል። በዚህም መሰረት ለጥር 7 ሁሉም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሚያዋጣቸውን አንድ አንድ ሰው መርጠው በመላክ 16 አባላት ያሉበት የኢትዮጵያ የሊግ ኩባንያ (PLC) ለመመስረት ትልቅ የመሰረት ድንጋይ የሚጣልበት ቀን ይሆናል። ይህ ለኢትዮጵያ እግርኳስም ትልቅ የመስራች ነው።” ብለዋል።

ሊጉ በአዲስ አካሄድ መከናወን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የውይይት እና ክርክር አጀንዳ ሆኖ የቆየውና ክለቦች ሊጉን አቋርጠው እስከመውጣት የደረሱበት ራሱን የቻለ የሊግ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ይቋቋማል ተብሎ ሲነገር ቢቆይም ክለቦች ሳይስማሙ በልዩነት እየወጡ ሳይሳካ ቀርቷል። የዚህ የሊግ የማስተዳደር ዕጣ ፈንታንም ሁሉም በጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ ነው።