ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር በዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታው ከወልዋሎ ነጥብ ተጋርቷል

ጅማ አባጅፋር በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በነበረው ተሳትፎ ምክንያት እስካሁን በሜዳው ጨዋታ ሳያደርግ የቆየው ጅማ አባ ደጅፋር በ8ኛ ሳምንት መርሐ ግብሩ ለመጀመርያ ጊዜ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል። ጨዋታውን ለመከታተል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና የቀድሞው የጅማ አባጅፋር ስራ አስኪያጅ የአሁኑ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሣይያስ ጂራ በስታድየሙ ታድመው ነበር።

በጅማ አባጅፋር በኩል ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረታው ስብስብ ውስጥ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ዐወት ገብረ ሚካኤልን በተስፋዬ መላኩ፣ መስዑድ መሐመድን በንጋቱ ገብረሥላሴ፣ ኄኖክ ገምቴሳን በኤልያስ ማሞ፣ ዲዲዬ ለብሪን በአስቻለው ግርማ እንዲሁም ማማዱ ሲድቤን በቢስማክ አፒያ በመተካት በ4-3-3 አሰላለፍ ለጨዋታው ሲቀርቡ በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በኩል በኢትዮጵያ ቡና 1-0 የተሸነፈውን ስብስብ ሳይቀይሩ በ 4-4-2 አቀራረብ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት። 

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመጀመርዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣን የአጨዋወትን ተመልክተናል። ወልዋሎዎች በቀኝ መስመር በእንየው ካሳሁን በሚሻገሩ ኳሶች ወደግብ ለመቅረብ ቢሞክሩም የሚሻገሩት ኳሶች በአባ ጅፋር ተከላካዮች በቀላሉ ሲመለሱ እና ኢላማቸውን ሲስቱ ተሰውሏል። በ9ኛው ደቂቃ እንየው ያሻማውን ሪችሞንድ ተቆጣጥሮት ወደ ግብ ሞክሮ በአባጅፋር ተከላካዮች ርብርብ ወደ ግብነት ሳይቀየር የቀረው ኳስ የሚጠቀስ ነው፡፡

ባለሜዳዎቹ በኤልያስ ማሞ፣ አስቻለው ግርማ፣ ይሁን እንደሻው እና ኤርሚያስ ኃይሉ አማካኝነት ኳስን ለደቂቃዎችች ቢያንሸራሽሩም ኳስን ከማንሸራሸር ያለፈ የጎል እድሎችን መፍጠር ተስኗቸዋል። ከክፍት ጨዋታ ይልቅ ከቆሙ ኳሶች ያገኟቸው አጋጣሚዎችም ኢላማቸውን ያልጠበቁ ነበሩ። በ4 ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ፣ በ6ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በተመሳሳይ በቅጣት ምት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ሲያደርጉ በ9ኛው ደቂቃ ተስፋዬ መላኩ ኳስን ለማሻማት ያሻገረው ኳስ አቅጣጫዋን ቀይራ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታካ ወጥታለች። በ11ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ ከኤርሚያስ ኃይሉ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ ለመግባት ሲሞክሩ ደስታ ደሙ አጨናግፎ ወደ ኃላ የመለሰውን ኳስ አብዱልአዚዝ በእጁ በመያዙ የእለቱ አልቢትር ለአብዱል አዚዝ የማስታወቂያ ካርድ ተሰጥቶ አባጅፋሮች ሁለተኛ ቅጣት ምት ቢያገኙም ኳሱን በትክክል ባለመቀባበላቸው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ያለው ጨዋታ ጊዜ አባጅፋሮች በአብዛኛው በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ላይ ቢያሳልፉም የጎል እድሎችን መፍጠር አልቻሉም። ኳሶች ሲቆራረጡና ኳስን ለማስጀመር በሚደረገት ጥረቶች ውስጥ አላስፈላጊ ጉሽሚያና ከዳኛው ጋር አላስፈላጊ እሰጣገባ ውስጥ ሲገቡም ነበር። በ22 ኛው ደቂቃ በንጋቱ ላይ በተሰራው ጥፍት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት አዳም ሲሶኮ የሞከረው አስደንጋጭ ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ እንዲሁም በወልዋሎ በኩል በ30 እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ እና አስራት መገርሳ በተመሳሳይ ከሳጥን ውጭ ያደረገቀቸው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በ43ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል ኤርሚያስ ሁለት ተጫዋቾችን አታሎ ቢስማርክ አክርሮ መሬት ለመሬት የመታውን አብዱልአዚዝ በሚገርም ብቃት አድኖበት ጨዋታው በማዕዘን ምት ቀጠለ ተብሎ ሲጠበቅ የእለቱ ዳኛ መደበኛው ሰዓት ሳይጠናቀቅ የመጀመሪያውን አጋማሽ ማለቂቃ ፊሽካ የነፉት መደበኛ ሰአት አለመጠናቀቁን ከአራኛው ዳኛ እንዲሁም ከእለቱ ኮሚሽነር ቢነገራቸውም በአቋማቸው በመፅናት መደበኛው ክፍለጊዜ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ወደ መልበሻ ቤት አቅንተዋል።

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ተዳክመው ታይተዋል። ባለሜዳዎቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ በቀጥተኛ ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ወልዋሎችም መጀመሪያ አጋማሽ ላይ አልፎም አልፎም በመስመር በኩል እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ሲያደርጓቸው የነበሩትን እቅስቃሴ በመተው ወደ ኃላ አፈግፍገው ለመጫወት መርጠዋል። ለዚህም እንዲረዳቸው 49ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስን በሮቤል በመቀየር የተከላካይ ክፍሉን ለማጠናከር እና በመስመር በኩል የአስቻለውንና የኤርሚያስን እቅስቃሴ ለመገደብ ችለዋል። አባጅፍሮች የመረጡት የአጨዋወት ከውጤታማነቱ ይልቅ በወልዋሎ ተከላካዮች በቀላሉ ሲመለሱ ከቆሙ ኳሶች የሚፈጥሯቸው የግብ እድሎችም ውጤታማ አልነበሩም። 

በ57ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ አስራት መገርሳን አታሎ ለማለፍ በሚሞክርበት ጊዜ በነበረ ንክኪ የእለቱ ዳኛ አስራት መገርሳን ቀጥታ በቀይ ካርድ በማስወጣት አወዛጋቢ ውሳኔ አስተላልፏል። ቀሪውን ክፍለ ጊዜ የቁጥር ብልጫ የያዙት ጅማ አባ ጅፋሮች ሰዓት በገፋ ቁጥር ይበልጥ ጫና ውስጥ እየገቡ የመጡ ሲሆን ጥቂት የግብ እድሎች ቢፈጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ተቀይሮ የገባው ማማዱ ሲድቤ በ70ኛው ደቂቃ ከግራ ወደቀኝ እያጠበ መጥቶ መሬት ለመሬት የሞከረውን አብዱል አዚዝ እንምንም ሲያድንበት በድጋሚ 79ኛው ደቂቃ ላይ ከድር ኸይረዲን ከመሀል ሜዳ ያሻማውን ማማዱ በግንባሩ ገጭቶ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣበት ሌላኛው ሊጠቀስ የሚችል ሙከራ ነበር። ከነዚህ ውጭ በረጅሙ ሲሻሙ የነበሩት ኳሶች ግብ ጠባቂው ሲሳይ ከመሆን ውጭ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡