የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-0 ወልዋሎ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት የዛሬ ብቸኛ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ከወልዋሎ ያለ ጎል አቻ ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል። 

” ተጫዋቾቹ ሜዳውን አለመልመዳቸው ተፅዕኖ አድርጎብናል ” ዩሱፍ ዓሊ – ጅማ አባጅፋር (ም/አሰልጣኝ)

ስለጨዋታው

” ያለፉትን ወራት ጨዋታዎችን ከሜችን ውጭ እንደማድረጋችን እና ተጨዋቾቹ ለሜዳው አዲስ እንደመሆናቸው መጠን ኳስን አንሸራሽረን እንዳንጫወት አድርጎናል። ተጫዋቾቹ ሜዳውን አለመልመዳቸው ተፅዕኖ አድርጎብናል። ተጋጣያችንም ሙሉ ለሙሉ ተከላክለው በመጫወታቸውም ግብ እን ዳናስቆጥር አድርጎናል። ”

ከእረፍት መልስ ስለተጠቀሙት የአጨዋወት መንገድ

” የተከተልነው የጨዋታ አቀራረብ ታክቲካል አልነበረም። ሜዳውን ካለመልመዳቸው የተነሳ እና ጎል ለማስቆጠር ካላቸው ጉጉት የተነሳ ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅመናል። ”

የጨዋታ መደራረብ

” ከግብፅ ከመጣን ጀምሮ ጨዋታዎችን ያለእረፍት በተደጋጋሚ እያደረገን እንገኛለን። እስከነ ጉዳታቸው ያሰለፍናቸው ተጨዋቾች አሉ። እንዲሁም የጉዳት ደረጃው ባይታወቅም በዛሬው ጨዋታ ሶስት ተጫዋቾች ተጎድተውብናል፡፡ ”

“ተጋጣሚያችን የመረጡት አጨዋወት ለኛ ተመችቶን ነበር” አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወልዋሎ

ስለ ጨዋታው

” ሁለታችንም ከሽንፈት እንደመምጣታችን የዛሬው ጨዋታ ለሁለታችንም ወሳኝ ነበር። ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈት ላለማስተናገድ ተጠንቅቀን ተጫውተናል። አስራት በቀይ ካርድ ከወጣ በኃላ ፎርሜሽናችንን ወደ 4-4-1 በመቀየር መጫወትን መርጠናል። ተጋጣሚያችን የመረጡት አጨዋወትም ለኛ ተመችቶን ነበር። ምክንያቱም የኛ ተከላካዮች በቁመት ከእነሱ አጥቂዎች ይሻሉ ነበር። የሚመጡትን የአየር ኳሶች በቀላሉ ስንቆጣጠር ነበር፡፡ ”

ስለ ዳኝነት 

” በዳኝነትቱ ደስተኛ አይደለሁም። ትከሻ ለትከሻ የተነካኩትን ነው በቀይ ካርድ ያስወጣብን። ረጅም ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች እንድንጫወት አድርጎናል። ይህ ደግሞ ጫና ውስጥ ከቶን ነበር። “