የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር እግርኳስ ፌዴሬሽን በከተማው ተቀማጭነታቸውን ካደረጉ በሁሉም የሊግ እርከኖች ተሳታፊ ከሆኑ ክለቦች ጋር ያሰናዳው የውይይት መድረክ እንዲሁም የ13ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ የማጠቃለያ ፕሮግራም ዛሬ በኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል ተካሂዷል፡፡
በከተማው መቀመጫቸውን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ክለቦች ተወካዮች በተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኃይለሰማዕት መርሐጥበብን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍሰሀ (ኢንጂነር) እና ሌሎች የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል። ከፌደሬሽኑ ኃላፊዎች ለውይይት መነሻነት በቀሩበት የተወሰኑ ነጥቦች ዙርያ ከተሳታፊዎች በርካታ ሀሳቦች ተነስተዋል። ለውይይት ከቀረቡት መነሻ ሀሳቦች መካከል ፌዴሬሽኑ ለክለቦች ስለሚያደርገው ድጋፍ፣ የማዘውተሪያ ቦታዎች ችግር እና የስፓርታዊ ጨዋነት ጉዳዮች ዋንኞቹ ነበሩ፡፡
ከተሳታፊዎች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በስፋት የተንጸባረቀው ሀሳብ የከተማዋ ክለቦች የመወዳደሪያ እንዲሁም መለማመጃ ሜዳ እጥረት እንዳለባቸውና ለዚህም በኪራይ ለውድድሮችና ልምምድ መስሪያ ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት እየተገደዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ሌላው ከተነሱ ሀሳቦች መካከል ፌደሪሽኑ በከተማው ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን አቅም ከመጠቀም እና አቅም ከመገንባት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት አንዳለ ተገልጿል። በተጨማሪም ከከተማው ትልቅነት አንጻር ፌደሬሽኑ ከሲቲ ካፕ ውድድር በዘለለ ሌሎች የገቢ መፍጠሪያ እድሎችን በመፍጠርና በመጠቀም ደረጃ ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉበት በተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡
በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሻቸውን የሰጡት አቶ ኃይለሰማዕት እንደተናገሩት የማዘውተሪያ ችግሮችን ለመፍታት በከተማው በሚገኙ 117 ወረዳዎች በተለዩ ክፍት ቦታዎች ላይ 117 መለስተኛ የእግር ኳስ ሜዳዎች ለመስራት ቦታዎች መለየታቸውንና ወደ ተግባር እየተገባበት የሚገኝ ሂደት መሆኑን ገልፀው በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር በአሁኑ ወቅት በእጁ የሚገኘውን ሜዳ የእግርኳስ ቡድኑን መልሶ የማያቋቋም ከሆነ ስለመንጠቀም እየታሰበ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ አያይዘው የከተማዋ ክለቦች ራሳቸውን ከሌሎች ክልል ክለቦች ጋር ማነፃፀር ተገቢ አለመሆኑንና በሌሎች ክልሎች ከእግርኳስ መርሆዎች ውጭ የሚካደውን አካሄድ ስለመከተል ከማሰብ ይልቅ ክለቦች ህዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸው መስራቱ የተሻለው አማራጭ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም በተነሱት ጥያቄዎች ዙርያ የሚመለከታቸው የፌደሪሽኑ አመራሮች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም 13ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊዎች የሽልማት እንዲሁም የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ ከውድድሩ ከተገኘው 1.81 ሚልየን ብር ጠቅላላ ገቢም ፌደሪሽኑ ከወጪ ቀሪ 1.3 ሚልየን ብር በውድድሩ ተሳታፊ ለነበሩ 8 ክለቦች በሽልማት መልክ ተበርክቷል፡፡
በዚህም ለውድድሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ማኅበራት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች የምስክር ወረቀትና ሽልማት በማበርከት የተጀመረው መርሐ-ግብሩ በእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ኃይለሰማዕት መርሐጥበብ አማካኝነት በውድድሩ ተካፋይ የነበሩ ቡድኖች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ፋሲል ከነማ፣ ወላይታ ድቻ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ አዳማ ከተማ ለተሳታፊነታቸው 81ሺህ 76 ብር ሽልማት ሲበረከትላቸው ውድድሩን በአራተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው መከላከያ የ108,101.78 ፤ በሶስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ጅማ አባጅፋር የ189,178.12፤ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ 405,381.68 እና 270,254.46 ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በተጨማሪም ለውድድሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበር የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በስተመጨረሻም የአዲስአበባ እግርኳስ ፌደሪሽን ለከተማው እግርኳስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ያላቸውን 5 ግለሰቦችን የእውቅና ሽልማት አበርክቷል፡-
1. ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ
2. ኑራ ኢማም
3. አሰልጣኝ ሰኢድ
4. አሰልጣኝ ግዛው
5. አቶ ጌታቸው አበበ የእውቅና ሽልማታቸውን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ከሆኑት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም እጅ ተቀብለዋል፡፡