በአማራ እና በትግራይ ክልል ክለቦች መካከል የሚደረጉ የኘሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በቀጣይ እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ፌዴሬሽኑ ለሚድያ በላከው መግለጫ መደበኛ የሊግ ጨዋታዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚካሄዱ የገለፀ ሲሆን በመጪው እሁድ መቐለ ላይ የሚደረገው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ የ9ኛው ሳምንት መደበኛ መርሐ ግብር አካል በመሆኑ የሚካሄድ ይሆናል። ፋሲል ከነማ በትላንትናው ዕለት ከትግራይ ክልል ክለቦች ጋር በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ ጨዋታ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።
የፌዴሬሽኑ ሙሉ መግለጫ የሚከተለውን ይመስላል፡-
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2011 ዓ.ም ኘሪምየር ሊግ ውድድር ኘሮግራም መሠረት በአማራ እና በትግራይ ክልል ክለቦች መካከል እንዲካሄዱ ኘሮግራም የወጣላቸው ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በመሆኑም የአማራ እና የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ስፖርት ኮሚሽኖች፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች በየክልላቸው ችግሮችን መፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ፣
1ኛ. ለተለያዩ ደጋፊ ማህበራት እና ደጋፊዎች እንዲሁም በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች ጉዳዩን አስመልክቶ ሥለተሰሩ ሥራዎች ጋዜጣዊ መግለጫዎችን የሰጡ መሆናቸውን፣
2ኛ. በየደረጃው ለሚገኙ የስፖርት ተቋማት እና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠታቸውን እና የቤት ሥራቸውን ማጠናቀቃቸውን
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የገለዱ ሲሆን ውድድሩን በተመለከተ በውድድሩ ኘሮግራም መሠረት በየክልሉ በመሄድ ጨዋታዎቻቸውን እንደሚያካሂዱ፣ እንግዳውን ቡድን በደማቅ ሁኔታ በመቀበል እና ተገቢውን መስተንግዶ በማድረግ ከጨዋታውም በኋላ በክብር እንደሚሸኑ መስማማታቸውን በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴም ክልሎቹ ያቀረቡትን በጐ ሃሳብ መሠረት በማድረግ መደበኛ የኘሪምየር ሊጉ ውድድሮች በወጣላቸው ኘሮግራም መሠረት የሚቀጥሉ ሲሆን የተስተካከይ ጨዋታዎቹ ኘሮግራም ቀጣይነት በቅርብ ጊዜያት በማውጣት የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን