ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር

ነገ ሀዋሳ ላይ በሚደረገውተስተካካይ ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ይገናኛሉ። በዚህ ጨዋታ ላይ ተከታዮቹን ነጥቦች ልናነሳ ወደናል።

የሰባተኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነበረው እና በጅማ አባ ጅፋር የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቶ የተላለፈው የሲዳማ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ተስተካካይ ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ይከናወናል። እስካሁን ሽንፈት ያልቀመሱት ሲዳማዎች ሳምንት በሮድዋ ደርቢ የከተማ ተቀናቃኛቸው ሀዋሳ ከተማን 1-0 መርታት ችለዋል። በዚህም የነጥብ ስብስባቸውን 12 በማድረስ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል። የቻምፒዮኖቹ አጀማመር ግን እንደአምናው ሁሉ ደካማ እየሆነ ይገኛል። በሜዳቸው ከወልዋሎ ጋር ያደረጉትን የመጀመሪያ ጨዋታም ያለ ግብ ለማጠናቀቅ ተገደዋል። ጅማዎች ገና አራት ጨዋታ ያደረጉ ቢሆንም አሁን 13ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ  በተስተካካይ ጨዋታዎቻቸው ግን የሊጉ መሪ የመሆን ዕድላቸው እንዳለ ነው።

በጨዋታው የሲዳማ ቡናው አጥቂ መሀመድ ናስር ከጉዳት የሚመለስ ሲሆን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በገጠመው የስብራት ጉዳት ከቡድኑ ጋር የሌለው ወጣቱ ሙጃይድ መሀመድ አሁንም ከጉዳቱ ተመልሶ ክለቡን ማገልገል ባለመቻሉ የነገው ጨዋታ ሙሉ የሜዳ ገቢ ለዚህ ተጫዋች እንዲሆን ክለቡ ወስኗል። በጅማ አባ ጅፋር በኩልም ዐወት ገብረሚካኤል ከጉዳቱ ቢመለስም ለዚህ ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለም ከረጅም ጊዜ ጉዳቱ አላገገመም። ከዚህ በተጨማሪ ያሬድ ዘውድነህ በግል ጉዳይ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልነበረ በመሆኑ ለዚህ ጨዋታ የማይደርስ ይሆናል።

በስድስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው አዲስ ግደይ አሁንም የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር አስፈሪው ጎን ነው። አዲስ  በጨዋታ ግብ ከማስቆጠር ባለፈም ለቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምቶች ምንጭ እየሆነ ይገኛል። ተጫዋቹ ከመስመር በመነሳት በተጋጣሚ የመሀል እና የመስመር ተከላካዮች መሀከል በመግባት የሚያሳድረው ጫና በነገውን ጨዋታ ለአባ ጅፋር የኋላ ክፍል ስጋት መሆኑ የሚቀር አይመስልም። አዲስ ከግራ መስመር እየተነሳ የሚያጠቃ ከሆነም በዐወት አለመኖር ምክንያት ለሳሳው የቻምፒዮኖቹ የቀኝ መስመር የተከላካይ ክፍል ፈተና ይሆናል።

በቁጥር ከሚስተካከሉት የተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል ጋር ብርቱ ፉክክር የሚጠብቃቸው የጅማ አማካዮች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድ ላይቸገሩ ይችላሉ። የሲዳማዎች ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ይህንን የበላይነት እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ነፃነት እንዲያገኙ ቢረዳቸውም የመስመር አጥቂዎቻቸው ትኩረት ግን በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ አለማግኘታቸውም ይህንን ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ለውጥ የሚደረግበት የቡድኑን ጠንካራ ጎን በነገው ጨዋታ አስተካክለው እንዲቀርቡ የሚያስገድዳቸው ነው። ትክክለኛውን ጥምረት ካገኙ ግን በሁለቱ ኮሪደሮች ወደ ሲዳማ ቡና የአደጋ ክልል ለመግባት ላይቸገሩ ይችላሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቻምፒዮኖቹ ወደ ሊጉ ባደጉበት የ2010 የውድድር ዓመት ቡድኖቹ ሁለት ጊዜ ሲገናኙ የመጀመሪያው ጨዋታ ጅማ ላይ ያለግብ የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛውን አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ 3-1 አሸንፏል፡፡

– ጅማ አባ ጅፋር ዘንድሮ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ውስጥ አንዱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ያለግብ ተለያይቷል፡፡

– ሲዳማ ቡና ሐዋሳ ላይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ በአንዱ ነጥብ ሲጋራ በቀሪዎቹ ድል አቀንቶታል፡፡

ዳኛ

– በሁለተኛው እና ስድስተኛው ሳምንት ሁለት ጨዋታዎችን በመምራት አስራአንድ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው ፌድራል ዳኛ ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ ለመዳኘት ተመደቧል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ዮናታን ፍሰሃ – ፈቱዲን ጀማል – ግርማ በቀለ – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ  – ዮሴፍ ዮሀንስ –ወንድሜነህ ዓይናለም

ፀጋዬ ባልቻ – ሀብታሙ ገዛኸኝ  –  አዲስ ግደይ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጄዬ

ተስፋዬ መላኩ – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ኄኖክ ገምቴሳ – ይሁን እንዳሻው – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ –  ቢስማርክ አፒያ – ማማዱ ሲዲቤ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *