በኬንያው ሻምፒዮን ጎር ማሂያ የሚጫወተው አማካይ ሃምፍሬ ሚዬኖ ስም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል። ከኬንያ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ፈረሰኞቹ የ29 ዓመቱን ተጫዋች የግላቸው ለማድረግ ጥብቅ ፍላጎት አላቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጫዋቹ እና ከክለቡ ጎር ማሂያ ጋር ድርድር እንደጀመረ የተሰማ ሲሆን ተጫዋቹንም ለማግኘት 15,000 ዶላር የዝውውር ክፍያ ማቅረባቸው ተነግሯል።
ሃምፍሬ ሚዬኖ በኬንያ እግርኳስን ለጀመረበት ኬሲቢ፣ ሶፋፓካ፣ ኤኤፍሲ ሊዮፓርድስ፣ ተስከር እና አሁን ለሚገኝበት ጎር ማሂያ የተጫወተ ሲሆን ከሃገሩ ወጥቶም በቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን እና በታንዛኒያው አዛም ክለቦች ቆይታ አድርጓል። ለኬንያ ብሔራዊ ቡድንም ላለፉት 8 ዓመታት በመጫወት ልምድ ያካበተ አማካይ ነው።
ጎር ማሂያ በናይጄሪያው ሎቢ ስታርስ ተሸንፎ ከቶታል ሻምፒዮንስ ሊግ ውጪ ከሆነበት ጨዋታ መልስ ተጫዋቹ ከቡድኑ ጋር ባለመገኘቱ ምናልባትም ክለቡን ለመልቀቅ በድርድር ላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። እንግሊዛዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ስቲዋርት ሃል ከሚዬኖ ጋር ከዚህ ቀደም በሶፋፓካ እና አዛም ክለቦች አብረው መስራታቸው ምናልባትም በፈረሰኞቹ ቤት ዳግም ሊገናኙ የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖር ይጠቁማል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሰናባቹ አሰልጣኝ ማኑኤል ቫስ ፒንቶ ጊዜ ካስፈረማቸው አምስት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ውስጥ በናይጄሪያዊው አጥቂ አሌክስ ኦሮትማል፣ ጋናዊው አማካይ ካሲሙ ታይሰን እና ቶጓዊው ተከላካይ ኢሱፉ ቡርሐና ብቃት ደስተኛ ባለመሆኑ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መፃፉ ይታወሳል። ክለቡ ከነዚህ ተጫዋቾች ጋር ሊለያይ እንደሚችል ሲጠበቅ እነርሱን ለመተካትም ለተወሰኑ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድል ሰጥቷል።