በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና በሜዳው ጅማ አባጅፋርን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡
ሲዳማ ቡና በ9ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ በግሩም አሰፋ እና ጸጋዬ ባልቻ ምትክ ሚሊዮን ሰለሞን እና ጫላ ተሺታ በመጀመርያ አሰላለፍ ሲያካትት ጅማ አባጅፋሮች በሳምንቱ መጀመርያ ከወልዋሎ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ቢስማርክ አፒያ፣ ኤልያስ ማሞ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ንጋቱ ገብረሥላሴን በማሳረፍ ለማማዱ ሲዲቤ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና ኄኖክ ገምቴሳ እድል በመስጠት ጨዋታውን ጀምረዋል።
የስራ ቀን በማይመስል መልኩ በበርካታ ደጋፊዎች የታጀበው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ጅማ አባጅፋሮችን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት የያዘን ባነር ለተጫዋቾቹ ከሰጡ በኋላ ሲጀመር መስዑድ መሐመድ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ ወደ ግብ መትቶ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ የጨዋታው ቀዳሚ የግብ አጋጣሚን የፈጠሩት ጅማ አባጅፋሮች የተሻለ አጀማመር ቢያደርጉም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ውስጥ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች በጅማ ላይ ብልጫን ማሳየት የቻሉበት ነበር። በዚህም ጅማዎች የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመከላከል ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ሲከተሉ ተስተውሏል።
ሲዳማዎች በተደጋጋሚ ወደ ጅማ የግብ ክልል ቢደርሱም በጋናዊው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጀይ አስደናቂ ብቃት ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ22ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ከድር ኸይረዲን የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ሐብታሙ ገዛኸኝ ያገኛትን ወርቃማ አጋጣሚ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ዳንኤል አጀይ በአስገራሚ ብቃት ያወጣበት ኳስም የሚጠቀስ ነበር። ሲዳማዎች ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ከመስመር በጫላ ተሺታ አማካኝነት በሚሻገሩ ኳሶች አደጋ መፍጠር ቢችሉም ከቀደመ እንቅስቃሴው ዛሬ ተቀዛቅዞ የታየው አዲስ ግደይ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል።
በጅማ አባጅፋር በኩል በ32ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት አስቻለው እና መስዑድ ባደረጉት ጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው ማማዱ ሲዴቤን ከግብ ጠባቂው ጋር ቢያገናኙትም ማሊያዊው አጥቂ የመታው ኳስ በ18ኛው ደቂቃ በጉዳት በወጣው ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ተተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ፍቅሩ ወዴሳ አውጥቶበታል። ሲዳማ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ጫን ብለው በሚጫወቱበት ወቅት ኃይልን ቀላቅለው ሲጫወቱ የነበሩት የጅማ ተከላካዮች በተደጋጋሚ ጥፋት ሲሰሩ የተሰዋለ ሲሆን በዚህም ሂደት በ43ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ በአዲስ ግደይ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ጅማዎችም ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጨረስ ተገደዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም በሚመስል መልኩ ተከላካዩ ዮናታንን በአማካዩ ወንድሜነህ ሲቀይሩ ጅማዎች ደግሞ ንጋቱ እና ቢስማርክን በማስገባት በረጃጅም ኳሶች ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የታየው ጫላ ተሺታ ኤልያስ አታሮን አታሎ ካለፈ በኃላ ወደ ግብ ክልል የላካትን ኳስ ሐብታሙ ገዛኸኝ አግኝቷት ወደ ግብ መትቶ የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጀይ መልሶታል። ከርቀት ግርማ በቀለ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም እና ዮሴፍ ዮሀንስ አክርረው የሞከሯቸው ኳሶችም ኢላማቸውን ሲስቱ እና የዳንኤል አጀይ ሲሳይ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። በጅማ በኩል 71ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ይሁን እንደሻው ከቀኝ የሲዳማ የግብ ክልል አሻግሮ ቢስማርክ አፒያ አግኝቷት በግቡ ብረት ስር ያለፈችበት ሙከራ የምትጠቀስ ናት።
በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች በራቸውን ዘግተው ሲጫወቱ የነበሩት ጅማ አባጅፋሮች በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራ በሲዳማ ብልጫ ቢወሰድባቸውም አስጠብቀው አንድ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። አዲስ ግደይ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እንዲሁም ወንድሜነህ ዓይናለም ከርቀት አክርረው በመምታት ያደረገቸው ሙከራዎችን አጄይ ሲያወጣቸው 83ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ተሺታ ወደ ግብ የላካት ኳስ አምበሉ ኤልያስ አታሮን ጨርፋ ከመረብ ልታርፍ ብትቃረብም የጨዋታው ኮከብ ዳንኤል አጀይ እንደምንም አወጣበት እንጂ በስተመጨረሻ ሲዳማን አሸናፊ ልታደርግ የምችልበት አጋጣሚ ነበረች።
ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ 90+3 ላይ በተደጋጋሚ የኃይል አጨዋወት ሲከተል የነበረው የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ዳግም ንጉሴ በቢስማርክ አፒያ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡
ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ደረጃቸውን ሳያሻሽሉ ሲዳማ 3ኛ፣ ጅማ 13ኛ ላይ ተቀምጠዋል።