ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ነገ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ደቡብ ፖሊስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በሚያደርጉትን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ሁለት ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አድርጎ ወደ ሀዋሳ የሚመለሰው ደቡብ ፖሊስ ከ2002 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያስተናግድበት የሊግ ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ ይጀምራል። ደደቢትን ብቻ በመብለጥ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ደቡብ ፖሊሶች ሁሉንም ጨዋታዎች ቢያከናውኑም አሁንም የሊግ ጉዟቸው ሊስተካከል አልቻለም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከድሬዳዋ ብቻ የገኙት አንድ ነጥብም ደረጃቸውን የሚያሻሽልላቸው አልሆነም። በሰባት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን የሰበሰበው ቅዱስ ጊዮርጊስም በሚፈልገው ፍጥነት እየተጓዘ አይገኝም። ሳምንት በሸገር ደርቢ ነጥብ የተጋሩት ፈረሰኞቹ እስካሁን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ የቻሏቸው ጨዋታዎች ሁለት ብቻ ናቸው። የነገው ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ በጊዮርጊስ ላይ በታሪክ የመጀመሪያ የሊግ ድሉን ለማግኘት ጊዮርጊስም በተጋጣሚው ላይ ያለውን የግንኙነት የበላይነት ለማስቀጠል የሚፋለሙበት ይሆናል።

ደቡብ ፖሊስ ከድሬዳዋ ከተማ ባደረገው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት የነበረው የተከላካይ አማካዩ ኤርሚያስ በላይ በነገ የሚመለስ ሲሆን የቀኝ መስመር ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለ ግን ከጉዳቱ ቢያገግምም ለነገው ጨዋታ እንደማይደርስ ታውቋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ መሀሪ መና  እና ምንተስኖት አዳነ አሁንም ከጉዳት ዝርዝር ውስጥ ያልወጡ ሲሆን ወደ ልምምድ የተመለሰው አሜ መሀመድ እና ሳለሀዲን በርጌቾም ወደ ሀዋሳ አልተጓዙም። ሙሉ ለሙሉ ያገገመው ጌታነህ ከበደ በአንፃሩ ሰፊ የጨዋታ ጊዜ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

ከአቀራረብ አንፃር ጨዋታው በሙሉ አቅሙ ለማጥቃት የሚሞክር ጊዮርጊስን እና ጥንቃቄ አዘል አካሄድን የሚመርጥ ደቡብ ፖሊስን እንደሚያስመለክተን ይገመታል። በእንቅስቃሴ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተመላላሾቹን በመጠቀም ለማጥቃት የሚያደርገው ጥረት የተሻለ ውጤታማ ሊያደርገው ቢችልም መሀል ለመሀል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ከመመከት ባለፈ የመስመር አጥቂዎቻቸውንም በመከላከሉ ላይ የሚያሳትፉት ደቡብ ፖሊሶች በቀላሉ በኮሪደሮቹ በኩል ክፍተት የሚሰጡ አይሆንም። በዚህም መሰረት በማጥቃት ሽግግር ወቅት የሚገኙ ክፍተቶችን በፍጥነት መጠቀም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ሲሆን ደቡብ ፖሊሶች ደግሞ መሀል ላይ ከሚያቋርጧቸው ኳሶች በፈጣን መልሶ ማጥቃት በፊት አጥቂው በኃይሉ ወገኔ አማካይነት የግብ ዕድሎችን ሊፈጥሩ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ያለው ከቆሙ ኳሶች አደጋ የመፍጠር ብቃት በተለይም የቀድሞው ክለቡን ከሚገጥመው አበባው ቡታቆ የሚነሱ ኳሶችን ለደቡብ ፖሊስ ልዩነት የመፍጠሪያ ጥሩ አማራጭ ያደርጋቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች አምስት ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ደቡብ ፖሊስ በሊጉ ጊዮርጊስን አሸንፎ አያውቅም፡፡

– በእርስ በርስ ግንኙነት ታሪካቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት ጎሎች ሲያስቆጥር ደቡብ ፖሊስ አንድም ጎል አስቆጥሮ አያውቅም፡፡

– ሀዋሳ ላይ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንዱን አቻ ተለያይተዋል፡፡

– ደቡብ ፖሊስ በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ ድል ሲቀናው በሶስቱ ሽንፈት ደርሶበታል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ በሁለት አጋጣሚዎች ከአዲስ አበባ የወጣ ሲሆን ማሳካት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ነው።

ዳኛ
– ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ ያደገው ፌደራል ዳኛ ዮናስ ካሳሁን ይህን ጨዋታ ይመራዋል። ዮናስ የኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ያደረጉትን ጨዋታ በመዳኘት ሦስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ዳዊት አሰፋ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ  – ዘሪሁን አንሼቦ – አበባው ቡታቆ

አዲስአለም ደበበ – ኤርሚያስ በላይ – ዘላለም ኢሳያስ

መስፍን ኪዳኔ  – በኃይሉ ወገኔ – ብሩክ ኤልያስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ለዓለም ብርሀኑ

ፍሬዘር ካሳ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ– ኄኖክ አዱኛ

አቡበከር ሳኒ

ሳላዲን ሰዓድ – አቤል ያለው

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *