የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅድመ ውድድር ዳሰሳ (ክፍል 1)

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን በነገው እለት ይጀመራል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም የሊጉ ክለቦችን በአጭሩ በመዳሰስ የውድድር ዘመናቸው ምን ሊመስል እንደሚችል ለማስቃኘት ትሞክራለች፡፡

Kidus Giorgis

1.ቅዱስ ጊዮርጊስ

ያለፈው አመት ደረጃ – ቻምፒዮን

ቁልፍ ግዢዎች – አስቻለው ታመነ እና ራምኬል ሎክ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – የለም

 

የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ በአዲስ አሰልጣኝ ፕሪሚየር ሊጉን ይጀምራል፡፡ ሆላንዳዊው ማርቲን ኩፕማን አምና ከግማሽ የውድድር ዘመን በኋላ የተሾሙ በመሆናቸው የቅዱስ ጊዮርጊስን አጨዋወት ፣ የተጫዋቾች ባህርይ እና የተጋጣሚዎችን ጠባይ ለመረዳት በቂ ጊዜ አግኝተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በመምራታቸው በሚፈልጉት መልኩ ቡድናቸውን ለማዘጋጀት እንዲችሉ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ ላይ 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ አሰልጣኝ ማርቲን በቡድኑ ላይ ከወትሮው የተለየ የአጨዋወት ባህርይ ለማስረፅ እየጣሩ እንደሆነ የአምበር ዋንጫ ማሳያ ሆኗል፡፡ ኳስን በመቆጣጠርላይ ያተኮረ ቡድን እየሰሩ ይመስላል፡፡

 

ጠንካራ ጎን

ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ የማሸነፍ ስነ ልቡናን እና ታሪካዊ የበላይነትን በሌሎች ክለቦች ላይ ይዟል፡፡ ቡድኑ አምና ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ መጥፎ የሚባል የውድድር አመት ቢያሳልፍም ዋንጫ ከማንሳት ያገደው አልነበረም፡፡ ዘንድሮ 80ኛ አመት በአሉን በዋንጫ ለማሳመር ይበልጥ ይነሳሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የቡድኑ የስብስብ ጥልቀት እና ጥራት አሁንም ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቻምፒዮንነት ቀዳሚ ተመራጭ እንድናደርገው ያስገድደናል፡፡ በሁሉም ቦታዋች የተሟላ የተጫዋች ስብስብን የያዘ ሲሆን በተለይ በመሃል ተከላካይ ስፍራ ላይ ብቻ 5 ጠራት ያላቸው ተጫዋቾችን ይዟል፡፡

የስብስብ ለረጅም ጊዜ አብሮ መቆየት ለአንድ ቡድን ውጤታማነት ወሳኝ ነው፡፡ ጊዮርጊስ ዘንድሮ ወደ ቡድኑ የቀላቀላቸው አዳዲስ ተጫዋቾች 2 ብቻ ሲሆኑ አመዛኞቹቹ ቢያንስ ለ4 አመት በቡድኑ የቆዩ ናቸው፡፡

ደካማ ጎን

በቅርብ አመታት ቡድኑ ላይ መታየት ያልቻለው የፈጠራ ችግር ዘንድሮም ሊደገም ይችላል፡፡ ቡድኑ ምንያህል ተሾመ በሚሰለፍባቸው ጨዋታዎች መሃል ለመሃል የሚደረጉ የማጥቃት አማራጭ ቢስተዋሉም ቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት በበኃይሉ አሰፋ ተሸጋሪ ኳሶች ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡

የቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ሌላው የቅዱስ ጊዮርጊስ ደካማ ጎን ነው፡፡ ቦታው ቋሚ ተጫዋች የሌለው ሲሆን በተደጋጋሚ የሚጎዳው አሉላ እና አቋማቸው የሚዋዥቀው ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ እንዲሁም አለማየሁ ሙለታን የያዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ መስመር አስተማማኝ አይደለም፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ውድድር ወደ ፊት የሚገፋ ከሆነ በሃገር ውስጥ ውድድር ላይ ያለውን ትኩረት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በ2005 ቡድኑ በፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ እስከ ምድብ ድልድል ሲደርስ ፕሪሚየር ሊጉን በመዘንጋቱ በቀጣዩ አመት በአፍሪካ ውድድር ላይ ሳይካፈል ቀርቷል፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ሮበርት ኦዶንግካራ

አሉላ ግርማ (አይዛክ ኢዜንዴ) ፣ አስቻለው ታመነ (ደጉ ደበበ) ፣ ሳላዲን በርጊቾ ፣ አበባው ቡታቆ (ዘካርያስ ቱጂ)

ምንተስኖት አዳነ ፣ ተስፋዬ አለባቸው (ናትናኤል ዘለቀ) ፣ ምንያህል ተሾመ

በኃይሉ አሰፋ ፣ ብሪያን ኡሞኒ (አዳነ ግርማ) እና ራምኬል ሎክ

Dedebit

2. ደደቢት

የአምና ደረጃ – 2ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – ተስሎች ሳይመን እና ሰለሞን ብሩ

የለቀቁ ወሳኝ ተጫዋቾች – ጋብሬል አህመድ እና ታደለ መንገሻ

ሰማያዊዎቹ ጦረኞች የውድድር ዘመኑን በስጋት እና ተስፋ ይጀምራሉ፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን ሲቀላቀሉ ለተጫዋቾች ያወጡት የነበረው የተጋነነ ወጪ አሁን የለም፡፡ ይልቁንም ወጪ ቆጣቢ ሆነዋል፡፡ ከብሄራዊ ሊጉን የማጠቃለያ ውድድር ተጫዋቾችን በአነስተኛ ወጪ የግል ለማድረግ ደደቢትን የቀደመ አልነበረም፡፡ ደደቢት ለዝውውር ያወጣው ከሌሎች ክለቦች በግማሽ የሚያንስ ነው፡፡

ቡድኑ ለፕሪሚየር ሊግ ውድድር አዲስ የሆኑ ተጫዋቾችን እና ከዚህ በፊት የፕሪሚየር ሊጉ የማሰልጠን ልምድ የሌላቸው አሰልጣኝ ከመያዙ በተጨማሪ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾችን ለቋል፡፡ ይህም የደደቢት የውድድር ዘመን ምን ሊመስል እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት እንዲያዳግት ያደርጋል፡፡

ጠንካራ ጎን

ደደቢት አምና ከውድድር ዘመኑ መጀመርያ ጀምሮ የማጥቃት አጨዋወቱ በንፅፅር ከሊጉ ክለቦች የተሻለ እንደነበር አሳይቷል፡፡ የደደቢት ተጫዋቾች ኳስን ባይቆጣጠሩም ኳስን በእግራቸው ስር ሲያደርጉ በፍጥነት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ አደጋ ይፈጥራሉ፡፡ የመስመር አጥቂዎችን እና የፊት አጥቂዎቹን ፍጥነት በአግባቡ ሲጠቀም የነበረው ደደቢት ዘንድሮ ይህንን ከደገመ ውጤታማ የውድድር አመት ሊያሳልፍ ይችላል፡፡

የአጥቂ መስመሩ በግብ አስቆጣሪዎች ድርቅ ከተመታው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአጥቂ ክፍል የተሻለው ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ እና የአምናው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሳሚ ሳኑሚ የደደቢት የአጥቂ ክፍልን ይመራሉ፡፡

ደካማ ጎን

ደደቢት ኮከቦችን ባለማስፈረሙና አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ለሊጉ አዲስ በመሆናቸው የቡድኑ ደረጃ እንደቀድሞው አይደለም፡፡ቋሚ ተሰላፊዎቹ ለዋንጫ የሚያፎካክር ብቃት ቢኖራቸውም ሙሉውን የቡድን ስብስብ ስንመለከት ለረጅሙ የውድድር ዘመን በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ታሪክ ጌትነት

ስዩም ተስፋዬ – ሰለሞን ብሩ (አክሊሉ አየነው) – አይናለም ኃይለ – ተካልኝ ደጀኔ

ሽመክት ጉግሳ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስሎች ሳይመን – ብርሃኑ ቦጋለ

ዳዊት ፍቃዱ – ሳሚ ሳኑሚAdama-Recovered1

3. አዳማ ከነማ

ያለፈው አመት ደረጃ – 3ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – ፋሲካ አስፋው እና ብሩክ ቃልቦሬ

ያጣቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – የለም

አዳማ ከነማ አምና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተመለሰ በኋላ 3ኛ ሆኖ የጨረሰበትን ምርጥ ውጤት ዘንድሮም ይደግመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጥንቃቄ እና መከላከልን የሚወዱት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የተረጋጋው ቡድናቸው ላይ ሰፊ ለውጥ ቢያደርጉም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ወሳኝ ተጫዋች ባለመልቀቃቸው በውድድር ዘመኑ ይቸገራሉ ተብሎ አይታስብም፡፡

ጠንካራ ጎን

የዝውውር መስኮቱ የስብስባቸውን ጥራት በአንድ ደረጃ አሳድጎላዋል፡፡ ቡድኑ ቶጓዊው ግብ ጠባቂ ጃኮብ ፣ ሞገስ ታደሰ ፣ እሸቱ መና ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ሲሳይ ባንጫን በማስፈረሙ አምና የተሞገሰላቸው የመከላከል አጨዋወታቸው ላይ የበለጠ ጥንካሬን ፈጥረዋል፡፡ ከሊጉ ምርጥ አማካዮች አንዱ የሆነው ብሩክ ቃልቦሬ እና አንጋፋው ፋሲካ አስፋው ምርጥ ግዢ ናቸው፡፡

በሜዳው ለማሸነፍ የሚከብድ ቡድን ነው፡፡ አምና በሜዳው ለመጀመርያ ጊዜ የተሸነፈው በመጨረሻው ጨዋታ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

አዳማ ጠንካራውን የተከላካይ ክፍል ይበልጥ ከማጠናከሩ በተጨማሪ የአማካይ መስመሩም በምርጥ ተጫዋቾች አሟልቷል፡፡ ወንድሜነህ ፣ ፋሲካ እና ብሩክን የያዘውን የአማካይ ክፍል አሰልጣኝ አሸናፊ በሚገባ ካዋሃዱ ከ2000 በኋላ የታየ ምርጡ አዳማ ከነማን ልንመለከት እንችላለን፡፡

ደካማ ጎን

የሌሎች ክለቦች ችግር የሆነው ሁነኛ አጥቂ ማጣት ለአዳማ ከነማም ፈታኝ ይሆናል፡፡ አምና 3ኛ ደረጃን ይዘው እንዲያጠናቅቁ የመስመር አጥቂው ዮናታን ከበደ ግቦች አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ አዳማ ጫላ ድሪባ እና ታፈሰ ተስፋዬን ቢያስፈርምም ታፈሰ እድሜው በመግፋቱ እና ተደጋጋሚ የጉዳት ሪኮርዱ ምክንያት በቋሚነት ቡድኑን መጥቀሙ አጠራጣሪ ነው፡፡ ጫላ ደግሞ በወጥነት ግብ የሚያስቆጥር አጥቂ አይደለም፡፡

ቡድኑ በርካታ የመሃል አማካዮችን በመያዙ በ4-4-2 አሰላለፍ ከዮናታን ከበደ ጎን የመስመር አጥቂው ታከለ አለማየሁን ሊያሰልፉ ይችላሉ፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ጃኮብ ፔንዲ

እሸቱ መና – ተስፋዬ በቀለ – ሞገስ ታደሰ – ሱሌይማን መሃመድ

ወንድሜነህ ዘሪሁን – ብሩክ ቃልቦሬ – ፋሲካ አስፋው – ተሾመ ሆሼ (ታከለ አለማየሁ)

ታከለ አለማየሁ ፣ ዮናታን ከበደ

Sidama Bunna

4. ሲዳማ ቡና

ያለፈው አመት ደረጃ – 4ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – አንተነህ ተስፋዬ እና ሙሉአለም መስፍን

ያጣቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – አብዱልከሪም መሃመድ

አምና አመዛኙን የውድድር ዘመን በድንቅ አቋም የዘለቀው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ በርካታ ተጫዋቾች አስፈርሞ የውድድር አመቱን ይጀምራል፡፡ አምና በውድድር ዘመኑ መገባደጃ ጨዋታዎች አቋሙ የወረደው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ ምን አይነት ለውጥ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መመልከት ያጓጓል፡፡

ጠንካራ ጎን

ስብስቡ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ከመዋቀሩ በተጨማሪ በክረምቱ እምብዛም ለውጥ አላስተናገደም፡፡ የቡድኑ ጠንካራ ጎን በሆነው የተከላካይ መስመር ላይ የአንተነህ ተስፋዬ መምጣት ተጨማሪ ጥንካሬን ይፈጥራል፡፡ አምና ምርጥ አማካይነቱን ያስመሰከረው ሙሉአለም መስፍን እና ሄይቲያዊው ሳውረን ኦልሪሽ በአካል ብቃት እና እድሜ የሳሳው የሲዳማ ቡና የአማካይ ክፍል ላይ አዲስ ሃይል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ደካማ ጎን

አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራው በደረሰባቸው የመኪና አደጋ ምክንያት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በረዳት አሰልጣኙ ቾምቤ ገ/ህይወት ለመስራት ተገድደዋል፡፡ የሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫን እንኳን ያካሄዱት በረዳት አሰልጣኙ መሪነት ነው፡፡ ይህም አሰልጣኝ ዘላለም ቡድናቸውን ለአዲሱ የውድድር ዘመን በሚፈልጉት መልኩ እንዳያዘጋጁ ያደርጋቸዋል፡፡

የአጥቂ መስመሩ እድሜ በገፉ ተጫዋቾች ተዋቅሯል፡፡ በክረምቱ ያስፈረሙትም ሌላውን አንጋፋ በረከት አዲሱን ነው፡፡ ቡድኑ አምና ከግማሽ የውድድር ዘመን በኋላ የተዳከመው በአንጋፋዎቹ የአካል ብቃት መውረድ ምክንያት ነበር፡፡ አዲስ ፈራሚው ላኪ ባሪለዱም ከአንጋፋዎቹ አንዱአለም ፣ በረከት እና ሙራንዳ ቀድሞ የመሰለፍ እድል ሊያገኝ ይችላል፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ለአለም ብርሃኑ

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – አወል አብደላ – ወሰኑ ማዜ

እንዳለ ከበደ – ሙሉአለም መስፍን – ፍፁም ተፈሪ – ሳውረን ኦልሪሽ

ኤሪክ ሙራንዳ (በረከት አዲሱ) – ላኪ ባሪለዱም (አንዱአለም ንጉሴ)

CBE_SA5. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አስደሳች ያልሆነ የውድድር ዘመን ጅማሮ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ ላይ የተመለከትነው ንግድ ባንክ ፕሪሚየር ሊጉን በብቃት ለመወጣት በደንብ መሻሻል ይጠበቅበታል፡፡ በክረምቱ ከፍተኛ ወጪ ያወጣው ቡድን ዘንድሮም እንደቀደሙት አመታት ከደረጃ በታች ሆኖ ሊጉን ከማጠናቀቅ በዘለለ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ፈተና ይጋፈጣል፡፡

ጠንካራ ጎን

ቡድኑ የያዛቸው ተጫዋቾች ለፕሪሚየር ሊጉ ፉክክር ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ ካስፈረማቸው በርካታ ተጫዋቾች መካከል ጋብሬል አህመድ ፣ ቶክ ጄምስ ፣ ቢንያም አሰፋ እና ፍቅረየሱስ ቡድኑን በሚገባ ሊጠቅሙ የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የባንክ ሌላ ጠንካራ ጎን የማጥቃት አማራጭ የሚያሰፉለት በርካታ ተጫዋቾች መያዙ ነው፡፡ ቡድኑ በቂ የመስመር አጥቂዎች እና የአጥቂ አማካዮች ከመያዙ በተጨማሪ አምና በከፍተኛ ግብ አግቢዎች ሰንጠረዥ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አጥቂዎች ባለቤት ነው፡፡

ደካማ ጎን

ንግድ ባንክ በየአመቱ ሽግግር ላይ የሚገኝ ቡድን ሆኗል፡፡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ቡድኑን ከተረከቡ ወዲህ ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን በመልቀቅ እና ማስፈረም ላይ አተኩሯል፡፡ ዘንድሮ ቡድኑን የተቀላቀሉት በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማዋሃድ ጊዜ መፈለጉ የማይቀር ነው፡፡

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ኢማኑኤል ፌቮ

አዲሱ ሰይፉ – ቶክ ጄምስ – ቢንያም ሲራጅ (አቤል አበበ) – አንተነህ ገ/ክርስቶስ

ጋብሬል አህመድ – ሰለሞን ገ/መድህን

ኤፍሬም አሻሞ (ሲሳይ ቶሊ) – አብዱልከሪም ሃሰን – ቢንያም አሰፋ (ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን)

ፊሊፕ ዳውዚ

Eth Bunna6 ኢትዮጵያ ቡና

ያለፈው አመት ደረጃ – 6ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – ዮሴፍ ዳሙዬ ፣ አብዱልከሪም መሃመድ ፣ እያሱ ታምሩ እና ሃሪንግተን ሃሱው

የለቀቁ ወሳኝ ተጫዋቾች – አስቻለው ግርማ ፣ ዳዊት እስጢፋስ እና ቢንያም አሰፋ

 

ቡና እና አሰልጣኝ ፖፓዲች በአዲሱ አመት መነጋገርያ ሆነው ሰንብተዋል፡፡ የአሰልጣኙ በኢትዮጵያ ያልተለመደ አጨዋወት ፣ በርካታ ተጫዋቾችን ለቀው እውቅና በሌላቸው ተጫዋቾች ላይ ማተኮራቸው የውይይት ርእስ ፈጥሯል፡፡

ጠንካራ ጎን

ያለፉት ጥቂት አመታት የቡድኑ ጠንካራ ጎን የነበረው የአማካይ ክፍል አሁንም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው፡፡ በመከላከል አጨዋወት ላይ ደከም ያለ ቢሆንም በፍጥነት እና ታታሪነት ላይ ላተኮረው ቡድን የሚስማሙ አማካዮች የያዘ ይመስላል፡፡ የመስመር ተከላካዮቹ እንደ አማካዮቹ ሁሉ ለማጥቃት አጨዋወት የሚስማሙ ናቸው፡፡ በአምበር ዋንጫው ላይ እንደታየው ደካማ ጎናቸው የነበረው የግብ ጠባቂ ችግራቸውን የፈቱ መስለዋል፡፡

የቡናን ጨዋታ የሚመለከቱ ተመልካቾች ቁጥር በዚህ አመት በአስገራሚ ሁኔታ መጨመሩ ታይቷል፡፡ ደጋፊው ዘንድሮም ከቡድኑ ውጤታማነት ጀርባ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ደካማ ጎን

አጥቂ እና ተከላካይ ክፍሉ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ተከላካይ መስመሩ መዋሃድ የሚጎድለው ሲሆን በአማካዮቹና በመስመር ተከላካዮቹየማጥቃት ባህርይ ምክንያት በቀላሉ ለጥቃት የተጋለጠ ነው፡፡ አጥቂ መስመሩ ላይ የሚሰለፍ እውነተኛ 9 ቁጥርም በቡና የለም፡፡

የስብስብ ጥልቀቱ ከአብዛኛዎቹ ክለቦች ያነሰ ነው፡፡ ለአድካሚው የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን የሚሆን ስብስብ ቡና ይዟል ማለት ይቸግራል፡፡ አሰልጣኙ በሚከተሉት በፍጥነት እና ታታሪነት ላይ ያተኮረ አጨዋወት ረጅሙን የውድድር ዘመን እንዴት እንደሚጨርሱ መገመት ያስቸግራል፡፡

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ሃሪንግተን ሀሶው

አብዱልከሪም አህመድ – ወንድይፍራው ጌታሁን – ኤፍሬም ወንድወሰን – አህመድ ረሺድ

እያሱ ታምሩ (መስኡድ መሃመድ) – ጋቶች ፓኖም – ዮሴፍ ዳሙዬ – ኤልያስ ማሞ

ጥላሁን ወልዴ – ያቡን ዊልያም (ሳዲቅ ሴቾ)

ArbaMinch Kenema

7. አርባምንጭ ከነማ

ያለፈው አመት ደረጃ – 7ኛ

ቁልፍ ግዢ – ታደለ መንገሻ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – አንተነህ ተስፋዬ እና ሙሉአለም መስፍን

 

በ2004 ወደ ፐሪሚየር ሊጉ ካደጉ ውዲህ የቻምፒዮንነት ተስፋ እና የመውረድ ስጋት የሌለበት በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚዋልል ቡድን ሆኗል፡፡ አርባምንጭ በክረምቱ አስቸጋሪ ጊዜን ያሳለፈ ክለብ ነው፡፡ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ማጣቱ እና ያለፉትን 4 አመታት ቡድኑን ካሰለጠኑት አለማየሁ አባይነህ ጋር መለያየቱ የውድድር ዘመኑን ሊያከብድበት ይችላል፡፡

ጠንካራ ጎን

ቡድኑ በየአመቱ መሻሻል ማሳየት የተሳነው በመሆኑ ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይልቅ በሌሎች ነገሮች ላይ ጥገኛ የሆነ ቡድን ሆኗል፡፡ አርባምንጭ በደጋፊው ብርታት በሜዳው ቢያንስ ነጥብ ተጋርቶ ይወጣል፡፡ አዲስ አበባ ላይም በበርካታ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ስለሚጫወት ነጥብ ይዞ የሚመለስባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች የአካባቢው ተወላጆች በመሆናቸው ለጨዋታ ያላቸው ተነሳሽነት የአርባምንጭ ጠንካራ ጎን ነው፡፡

ደካማ ጎን

የስብስብ ደረጃው ከአመት አመት እየወረደ ነው፡፡ አምና በሰንጠረዡ ወገብ እንዲጨርሱ ያስቻላቸው የአንተነህ እና ሙሉአለም አቋም ቢሆንም አሁን በቡድኑ የሉም፡፡ ከታደለ መንገሻ በቀር ይህ ነው የሚባል ግዢ አልፈፀመም፡፡

ቡድኑ ከአሰልጣኝ አለማየሁ ስንብት በኋላ መሪ የሌለው መስሏል፡፡ ቡድኑን በጊዜያዊነት የተረከቡት አሰልጣኝ መለሰ ሸመና ከጊዜው ጋር የሚራመዱ አይነት አሰልጣኝ አይደሉም፡፡ የአሰልጣኙ ወርቃማ ጊዜ ያለፈው በ1995 አርባምንጭ ጨርቃጨርቅን በፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ከረዱ በኋላ ነው፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

አንተነህ መሳ

ታገል አበበ – በረከት በጋለ – አለማየሁ ሽብሩ – አበበ ጥላሁን

አማኑኤል ጎበና – ምንተስኖት አበራ – ትርታዬ ደመቀ – ታደለ መንገሻ

ተሾመ ታደሰ – በረከት ወ/ፃዲቅ


 

(ይቀጥላል…)

ያጋሩ