በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ከተረታ በኃላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንዲህ ሰጥተዋል።
ስቴዋርት ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለ ጨዋታው
ጥሩ ተጫውተናል ብዬ አላስብም። እነሱ ኳሱን ተቆጣጥረውት ነበር። እኛ በአስራ አንድ ቀን አራት ጨዋታ ነው ያደረግነው። በዚ ምክንያት ዛሬ በጉልበት መጫወት ከብዶናል። ከዛ በተጨማሪ አንድ ተጫዋች ቅጣት ላይ አራት ተጫዋቾች ደሞ ጉዳት ላይ ነበሩ። በዚ ምክንያት አማራጮቻችን በጣም ጠበዋል።
” ባለፉት ጨዋታዎች ግብ ይቆጠርብን ነበር። ዛሬ ግን ሶስቱም የመሃል ተከላካዮቻችን ጥሩ ነበሩ።
” ጥሩ ጥሩ የአጥቂ ክፍል ተጫዋቾች ስላሉን ብዙ ግብ አግብተን ማሸነፍ እንችል ነበር። ግን አጥቂዎቻችን ከጉዳት ነው የመጡት። በዛላይ አቤል ብቻውን ስለነበር የጨዋታ መደራረቡም ነበረበት። ሳልሃዲን ጉዳት ላይ ነበር፣ ጌታነህ ደሞ ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ጉዳት ላይ ነው ያለው፤ አሜ መሐመድም በተመሳሳይ.. አጥቂዎቻችን በሙሉ ጤና ካገኙ ብዙ ግብ አግብተን እናሸንፋለን።”
ስለ ሊጉ ፉክክር
ጥር ላይ ማንም ዋንጫ አንስቶ አያውቅም። በእጃችን ጨዋታዎች ስላሉ እነሱን ማሸነፍ አለብን። አብዛኛው ቡድን ተደጋጋሚ ነጥብ እየጣለ ነው። ፉክክሩ ለማንም ክፍት ነው። ”
ያለው ተመስገን – የደቡብ ፖሊስ ረዳት አሰልጣኝ
ግብ የማስቆጠር ክፍተት እና የጨዋታው እንቅስቃሴ
” የተሻለ ተንቀሳቅሰን እናሸንፋለን ብለን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። እንቅስቃሴያችን ጥሩ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር አልቻልንም። ይህ ከዚህ በፊትም የኛ ዋነኛ ችግር ነው። ይህን ደግሞ መቀየር እንችላለን። ማስቆጠር አቅም ያላቸው አሉ፤ ቶሎ የመድረስ አቅምም ያላቸው ልጆች በቡድኑ ውስጥ አሉ። እኚህን ሁሉ ለመቅረፍ ደግሞ ጠንክረን እንሰራለን። ”
ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ ቡድኑ ውስጥ ስላለው የተለየ ነገር
” ቡድኑ ውስጥ ከበስተጀርባ ያሉ ችግሮች ብዙ የሉም። ቡድኑ ውስጥ ያለው መልካም የሆነ ግንኙነት ነው። በሜዳም ከሜዳም ውጭ ለማሸነፍ ያለን ተነሳሽነት የተሻለ ነው። አንዳንዴ የማሸነፍ ትራክ ውስጥ መግባት ካልቻልክ ከባድ ነው። እነዚህ ደግሞ በተጫዋቾቹ አዕምሮ ተፅዕኖ አድርጓል። ለተደጋጋሚ ሽንፈቱ ደግሞ እነዚህ እንደ አንድ ችግር ሊቆጠር ይችላል። ወደ ማሸነፍ ከመጣን ደግሞ እነዚህን መቅረፍ ይቻላል። በአጠቃላይ እኛ በምንፈጥረው ስህተት እንጂ የሚቆጠርብን የአቅም ችግር የለብንም።”