የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጀምር 11 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም መከላከያን የገጠመው አዳማ ከተማ 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ ዳዋ ሆቴሳ አራት ግቦችን አስቆጥሯል።
መከላከያ ባሳለፍነው ሳምንት በባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ከባህር ዳር ከተማ ጋር 1-1 ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ላይ ሽመልስ ተገኝ እና አበበ ጥላሁንን በምንተስኖት ከበደ እና ዓለምነህ ግርማ ሲተኩ አማካይ ስፍራ ላይ በኃይሉ ግርማን በቴዎድሮስ ታፈሰ በመቀየር ቀርበዋል። በአንጻሩ አዳማ ከተማዎች ደቡብ ፖሊስን በሜዳው 1-0 ከረታው ቡድን ውስጥ ተከላካዩ ሱለይማን መሀመድን እና አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩን አስወጥተው ቴዎድሮስ በቀለን እና ከነዓን ማርክነህን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ አምጥተዋል።
ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው ገና በ4ኛው ደቂቃ ነበር። ይድነቃቸው ኪዳኔ ከግብ ክልሉ በወጣበት አጋጣሚ አዲስ ህንጻ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም ቀድሞ ወደ ቦታው የተመለሰው ይድነቃቸው ኪዳኔ አድኖበታል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አዳማዎች የመከላከያ ተከላካዮችን ጫና ውስጥ በመክተት ስህተቶችን እንዲሰሩ ለማስገደድ ሲሞክሩ በአንጻሩ መከላከያዎች ደግሞ የአዳማን የመከላከል አደረጃጀት መሀል ለመሀል ሰብሮ ለመግባት ጥረት አድርገዋል፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት አዳማዎች በ21ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከነዓን እና ቡልቻ በፈጠሩት ቅንጅት በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ መከላከያ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ ከነዓን በድንቅ ሁኔታ ሲያሳልፍለት በረከት ደስታ ተረጋግቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡
ነገር ግን በደቂቃዎች ልዩነት በ25ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ከቀኝ መስመር ወደ አዳማ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ ከምኞት ደበበ ጋር ታግሎ ወደ ውስጥ ሊያሻግረው የነበረውን ኳስ ተስፋዬ በቀለ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ምንይሉ በመምታት አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከአቻነት ግቧ መቆጠር በኃላ አዳማ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል በዚህም በ28ኛው ደቂቃ ከነዓን ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ አዲስ ህንጻ በግንባሩ ገጭቷት ወደ ውጪ የወጣችበት እንዲሁም በ41ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ይድነቃቸው ያዳነበት ኳሶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለተመልካች ሳቢ በነበረው በዚሁ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች መሪ ሊሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ የግቡ ቋሚ ከልክሏቸዋል፡፡
በ35ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ የተመለሰበት አጋጣሚ እንዲሁም በ44ኛው በአዳማዎች በኩል ቡልቻ ሹራ በአስገራሚ መልኩ ያቀበለውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ተጠቅሞ በረከት ወደ ግብ ቢሞክርም በተመሳሳይ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡
1-1 የተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያዎች አጋማሽ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም የተለየ መልክ ነበረው፡፡ በ51ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በቀጥታ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ በመምታት አስቆጠሮ ቡድኑን ዳግም መሪ ማድረግም ችሏል፡፡ ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ በደቂቃዎች ልዩነት በ54ኛው ደቂቃ የመከላከያው ተመስገን ገብረኪዳን ኢስማኤል ሳንጋሪን በቡጢ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፤ ይህም የጨዋታውን መንፈስ ሙሉ ለሙሉ የቀየረ አጋጣሚ ሆኗል፡፡
ከአንድ ተጫዋች መጉደል ጋር ተያይዞ አዳማዎች ይበልጥ ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለው በ60ኛው ደቂቃ ቡልቻ ሹራ አራት የመከላከያ ተጫዋቾች አልፎ ወደ መከላከያ ሳጥን ከደረሰ በኃላ ወደ ግብ የላከው ኳስ በይድነቃቸው ሲመለስ በቅርብ የነበረው በረከት ደስታ ዳግም ወደ ግብ የላካውን ኳስ በዓለምነህ ግርማ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ማስቆጠር ችሏል ፤ ዓለምነህ ግርማም በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡
በመቀጠል በ69ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ በፈጣን ሽግግር ከግራ መስመር ያሻገለትን ኳስ ዳዋ ሆቲሳ በግንባሩ በመግጨት ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በ8 ተጫዋቾች እንደመጫወታቸው መከላከያዎች የግብ ልዩነቱን ይበልጥ እንዳይሰፋ በማሰብ ፍሬው ሰለሞንን ቀይረው በማስገባት ኳስን ተቆጣጥረው የጎንዮሽ እና የኋልዮሽ ቅብብሎችን በርከት በማድረግ ሌላ ግብ ላለማስተናገድ ጥረት አድርገዋል፡፡ በአዳማዎች በኩል በረከት ደስታ ሱራፌል ዳንኤል እንዲሁም ከነዓን ማርክነህ ተጨማሪ ግብ ሊያገኙባቸው የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች አምክነዋል ፤ ነገርግን በጨዋታው ኮከብ የነበረው ዳዋ ሆቴሳ ለራሱ አራተኛ ለቡድኑ ደግሞ አምስተኛ እና ማሳረጊያ የሆነችውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በእንግዶቹ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።