ከነገ ጨዋታዎች መካከል ዘግየት ብሎ የሚጀምረው የቡና እና የሽረ ጨዋታን የተመለከተው ቅደመ ዳሰሳችን እንደሚከተለው ይነበባል።
ሳምንት ከከተማ ተቀናቃኙ ጋር ያለግብ የተለያየው ኢትዮጵያ ቡና ደካማ አቋም እያሳየ የሚገኘው ስሑል ሽረን በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያስተናግድበት የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ ነገ 10፡00 ላይ ይጀምራል። ኢትዮጽያ ቡና እስካሁን በሰበስባቸው 15 ነጥቦች ሀዋሳን አስከትሎ ሊጉን በመምራት ላይ ሲገኝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ካደረገው የመጨረሻ ጨዋታ አስቀድሞ ሁለት ተከታታይ ድሎችን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መዲናዋ የሚመጡት ስሑል ሽረዎች አሁንም ሙሉ ነጥቦችን ማሳካት ተስኗቸው ይገኛሉ። ከደቡብ ፖሊስ እና ደደቢት ብቻ ተሽለው 14ኛ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ያስቻሏቸው አምስት ነጥቦችም የተገኙት ከአቻ ውጤቶች ነበር።
ኢትዮጵያ ቡና አስራት ቱንጆን እና ሳምንት ጉዳት ያስተናገደው አምበሉ አማኑኤል ዮሃንስን ሲያጣ ልምምድ የጀመረው ኃይሌ ገብረትንሳይን ግን ከጉዳት መልስ ያገኛል። በስሐል ሽረ በኩል ደግሞ መብርሀቶም ፍስሃ ፣ ሸዊት ዮሃንስ ፣ ደሳለኝ ደባሽ ፣ ሰይድ ሃሰን እና ሃፍቶም ቢሰጠኝ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ሲሆን ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ ከቅጣት ሰለሞን ገብረመድህን እና ንስሃ ታፈሰ ደግሞ ከጉዳት መልስ ቡድኑን እንደሚያገለግሉ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከመጡበት መንገድ አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ ቡና የበላይ ሆኖ ሊጨርስ የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ መናገር ይቻላል። በጊዮርጊሱ ጨዋታ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገው የገቡት ቡናዎች በነገው ጨዋታ ወደ ቀደመው 4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ እንደሚመለሱም ይታሰባል። ከወላይታ ድቻው ጨዋታ በኋላ በክፍት ጨዋታ ግብ ያላስቆጠሩት ቡናማዎቹ በሜዳው ስፋት በመከላከሉ ደክሞ የሚታየውን የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል በመስመር ተከላካዮቻቸው ተሳትፎ በማስከፈት ከሁለቱ አጥቂዎቻቸው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚጥሩ ይገመታል። ወደ ተጋጣሚው የመከላከል ዞን የተጠጋ የአማካይ ክፍል እና ከግብ ክልሉ ርቆ የሚከላከል የኋላ መስመርም ነገ ከዲዲዬ ጎሜስ ስብስብ የሚጠበቅ አቀራረብ ነው።
በራሳቸው ሜዳ መቅረትን ምርጫቸው ሊያደርጉ የሚችሉት ሽረዎች የመከላከል ክፍተታቸውን አርመው ካልገቡ ከሜዳ ውጪ ያላቸው አስከፊ ሪከርድ ሊቀጥል የሚችልበት አጋጣሚ መፈጠሩ አይቀርም። ለተከላካይ መስመራቸው በቂ ሽፋን ከመስጠት ባለፈም የቡናን የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች እንቅስቃሴን የማቋረጥ እና ማጥቃትን በማስጀመር ሂደት ላይ እነኄኖክ ካሳሁን የሚኖራቸው ስኬት ቡድኑ የግብ ዕድሎችን እንዲያገኝ እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል። ነገር ግን የፊት አጥቂውም ሆነ ከእርሱ ብዙ ርቀው ሊገኙ የሚችሉት አማካዮች ከተጋጣሚያቸው የመከላከል መስመር ጀርባ በስኬታማ ቅብብሎች እና በፍጥነት ለመግባት የብቃታቸው ደረጃ ከፍ ብሎ ሊገኝ ግድ ይላል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ጨዋታው በሁለቱ ተጋጣሚዎች መካከል እርስ በርስ የሚደረግ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ነው።
– ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ላይ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሦስቱን አሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። የነገው ጨዋታ ለቡና አራተኛ ተከታታይ የአዲስ አበባ ጨዋታ ይሆናል።
– ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጪ ያደረጉት ስሑል ሽረዎች በድምሩ አስር ግቦችን አስተናግደው ሁለቱንም ተሸንፈዋል።
ዳኛ
– ይህ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ይመራዋል። ዳዊት እስካሁን በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች ስምንት የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን አሳይቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)
ዋቴንጋ ኢስማ
አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ተካልኝ ደጀኔ
ዳንኤል ደምሴ
ካሉሻ አልሀሰን – ሳምሶን ጥላሁን
ሚኪያስ መኮንን
ሱለይማን ሎክዋ – አቡበከር ነስሩ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ሰንደይ ሮቲሚ
አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ
ሳሙኤል ተስፋዬ – ኄኖክ ካሳሁን
ልደቱ ለማ – ጅላሎ ሻፊ – ኪዳኔ አሰፋ
ሚድ ፎፋና