የ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በዛሬው ዕለት ጅማሮውን አድርጓል። 17 ክለቦች ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ ውድድር ዛሬ ስድስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።
ምድብ ሀ
ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው መከላከያ ሜዳ መከላከያ ከአንድ ጊዜ የውድድሩ ቻምፒዮን ሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ፈጠን ያለው እና ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ መጀመሪያ ሀዋሳዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው የታዩበት ነበር። ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ውስጥ በመጣል በተለይም በግራ በኩል ጫና ፈጥረው በመጫወት በዛው አቅጣጫ በሚያጠቃው ሀብታሙ መኮንን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት መከላካዮች ግን በአጫጭር ቅብብሎች ተጋጣሚያቸውን ወደ ራሱ ግብ ገፍተው የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመውሰድ ለረጅም ደቂቃዎች ብልጫ አሳይተዋል።
ከግራ መስመር ተከላካዩ መሳፍንት ጳውሎስ በሚነሱ ኳሶች እንዲሁም በመስመር አማካዩ መሀመድ አበራ ፍጥነት በመታገዝም ሰብረው ለመግባት ብዙ ሞክረዋል። ነገር ግን ግብ በማግባት ቀዳሚ የሆኑት በቀላሉ የኋላ መስመራቸውን ያልከፈቱት ሀዋሳዎች ነበሩ። 25ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግራ ማስመር ያደላውን የርቀት ቅጣት ምት ሀብታሙ ሲያሻማ የጦሩ የመሀል ተከላካይ ይሁን ብሩክ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል። በቀጣይም ሀዋሳዎች በአጥቂዎቻቸው መስፍን ታፈሰ እና ተባረክ ኢፋም የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም በእንቅስቃሴ ግን እጅግ ተሽለው የታዩት መከላካየዋች ነበሩ። 35ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ተፈራ እንዳለ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ እና 45ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ አሻምቶለት አምበሉ ሰለሞን ሙላው በግንባር የሞከረው ኳስም የቡድኑ ጠንካራ ሙከራዎች ነበሩ።
ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽም የቡድኖቹ ፉክክር ከፍ ብሎ የታየበት ነበር። በተለይም የመጀመሪያ አጋማሽ ብልጫቸውን ማስቀጠል የቻሉት እና ወደ ቀኝ መስመር ባደላ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ደጋግመው ይገቡ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ጎልተው ወጥተዋል። የዚሁ ቦታ ተሰላፊ የሆነው ሠለሞን ሙላው 50ኛው ደቂቃ ላይ ያሻማውን ኳስ የፊት አጥቂው አቤል ነጋሽ በግንባሩ የገጨበት አጋጣሚም ጥሩ ሆኖ በዋለው የሀዋሳው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ የተመለሰ ነበር። ሆኖም 54ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሜ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ አቤል በግንባሩ ሞክሮ አላዛር ሲያድንበት ሰለሞን ደርሶ በድጋሜ ሞክሮ ቢመልስበትም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ግብ የላከው ኳስ ግን ወደ ግብነት ተቀይሯል።
ከአቻነት ግቧ በኃላ ሀዋሳዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ከሞከረው ኳስ በኋላ መስፍን ታፈሰ እና ተቀይሮ የገባው ምንስተኖት እንድርያስ ሁለት ጊዜ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝተው ስተዋል። በአማካዮቻቸው ዊሊያም ሰለሞን እና ተፈራ እንዳለ ድንቅ ብቃት በመታገዝ ኳስ ይዘው ሲጫወቱ የነበሩት መከላከያዎች ግን በጨዋታ እንቅስቃሴ የተሻሉ ሆነው መታየታቸው አልቀረም። የፊት አጥቂው አቤል ነጋሽ ሌላ የግንባር ኳስም ለጥቂት ነበር በአላዛር ግብ ከመሆን የዳነው። በተለይም የሀዋሳው የመሀል ተከላካይ ፀጋአብ ዮሀንስ 86ኛው ደቂቃ ላይ ባልተገባ ባህሪ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ መከላከያዎች በዊልያም ፣ ሰለሞን እና በተከላካይ አማካዩ ኩራባቸው ቢዘልቅ ከሳጥን ውጪ ጠንካራ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በሌሎች የምድቡ ጨዋታዎች አካዳሚ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን ገጥሞ 1-0 ሲያሸንፍ ወደ አሰላ ያመራው የአምናው ቻምፒዮን ወላይታ ድቻ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 3-1 አሸንፏል።
በዚሁ ምድብ ነገ ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ ላይ በ4:00 ቅደለስ ጊዮርጊስ ከ አምቦ ጎል ፕሮጀክት፤ ሀዋሳ ላይ በ9:00 ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።
ምድብ ለ
24 ሜዳ ላይ በ4:00 በዚህ ውድድር ላይ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ የሆኑት አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን እና ፋሲል ከነማን ያገናኘው ጨዋታ በአፍሮ ጽዮን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው አፍሮ ጽዮኖች እንቅስቃሴያቸው በማጥቃት ወረዳ ላይ ሲደርስ በቀላሉ ሲጨናገፍ ተስተውሏል። በዚህም በዚህ አጋማሽ የጠሩ የግብ እድሎች መፍጠር የቻሉት በጥቂት አጋጣሚዎች ነበር። በ12ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት ይዘው የሄዱትን ኳስ ፊሊሞን አማራ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ መትቶ የግቡ ቋሚን ለትሞ የተመለሰበት ኳስ እንዲሁም በ24ኛው ደቂቃ ናትናኤል እንዳዘዘው ከተመሳሳይ ቦታ ሞክሮ የፋሲል ግብ ጠባቂን ጨርፎ አግዳሚው የመለሰባቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። እንግዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች በመጀመርያው አጋማሽ ከራሳቸው የሜዳ ክልል ብዙም ሳይርቁ መጫወትን የመረጡ ሲሆን ከርቀት ከሚሞከሩ ኳሶች ውጪ አፍሮ ፅዮኖችን የሚፈትን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት አፍሮ ጽዮኖች በቶሎ ጎል ማግኘት ችለዋል። በ51ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፊሊሞን አማረ ያስቆጠራት ጎልም የጨዋታውን ውጤት የለወጠች ሆናለች። ከጎሉ በኋላ ፋሲሎች የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም በአፍሮ ፅዮን የግብ ክልል የተገኙባቸው ቅጽበቶች እጅግ ጥቂት ነበሩ። በዚህም ከርቀት ከየትኛውም አቅጣጫ ኢላማቸውን ያልጠበቁ በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። አፍሮ ጽዮኖችም በመልሶ ማጥቃት የጎል እድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በአፍሮ ጽዮን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
* ጨዋታው የተደረገበት የ24 ሜዳ እጅግ ከፍተኛ የሆነ አቧራ ለቡድኖቹ እንቅስቃሴ፣ ለተመልካችም ጨዋታውን በአግባቡ ለመከታተል አዳጋች እንደሆነ ታዝበናል። ፌዴሬሽኑም ጨዋታዎቹን ለውድድሩ ደረጃ በሚመጥን ቦታ ላይ በማድረግ ረገድ ስራዎች ሊሰራ እንደሚገባ ያሳየ ሆኖ አልፏል።
በዚህ ምድብ ሌሎች ጨዋታዎች ወልቂጤ ላይ ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-1 ሲለያዩ አሰላ ላይ ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ከአዳማ ከተማ ያለ ጎል ነጥብ ተጋርተዋል። መድን ሜዳ ላይ ሊደረግ የነበረው የመድን እና ሀላባ ከተማ ጨዋታ ሀላባዎች እና የእለቱ ዳኞች በቦታው ቢገኙም ባለሜዳው በለድን ባለመገኘቱ ሳይከናወን ቀርቷል። ስለ ጉዳዩ ከመድን ክለብ ባገኘነው ምላሽ የተጫዋቾቻቸውን የMRI ውጤት ፌዴሬሽኑ ተመልክቶ እስካሁን ምላሽ ባለመስጠቱ ጨዋታውን እንዳላከናወኑ ገልጸዋል።