ኤሌክትሪክ ከ መከላከያ – ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ሰአት – 09፡00

ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም


 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታ በመከላካያ እና ኤሌክትሪክ መካከል ነገ በ9፡00 ይካሄዳል፡፡ አምና በተመሳሳይ በመጀመርያ ሳምንት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ነገ ከሚደረገው ጨዋታ በፊት ስለ ዝግጅታቸው የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በመጀመርያ ሳምንት ነጥቦችን መሰብበስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ እየተዘጋጀን ያለነው ለመክፈቻ ጨዋታ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉንም ጨዋታዎች ውጤታማ ሆኖ ለመጨረስ ነው አላማችን፡፡ ነገር ግን የመጀመርያዎቹ 2 ሳምንታት የምታስመዘግበው ነጥብ ወሳኝነት አለው፡፡ ከተወሰኑ ጨዋታዎች በኋላ ውድድሩ የሚቋረጥ በመሆኑ ነጥቦችን ቀድሞ መሰብስቡ ወሳኝ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ መከላከያ በርካታ አጥቂዎችን የያዘ ሲሆን የአጥቂ አማራጫቸውን በአግባቡ እንደሚጠቀሙ አሰልጣኝ ገብረመድህን ተናግረዋል፡፡

‹‹ አጨዋወታችን በማጥቃት ላይ ቢሆንም ያሉኝን አጥቂዎች በሙሉ መጠቀም አንችልም፡፡ እንደ የጨዋታው አይነት በምንቀያይረው ሲስተም አጥቂዎቹን እጠቀምባቸዋለሁ›› ብለዋል፡፡

መከላከያ በነገው ጨዋታ የጀማል ጣሰው ፣ ሚልዮን በየነ እና ሙሉአለም ጥላሁንን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም፡፡

የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ በአምበር ዋንጫ ባሳዩት ደካማ አቋም ፕሪሚየር ሊጉን እንደማይጀምሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹ ከመክፈቻው የመከላከያ ጨዋታ በዘለለ ለሁሉም ጨዋታዎች ተዘጋጅተናል፡፡ የአምበር ዋንጫው ድክመቶቻችንን ለማየት ጠቅሞናል፡፡ የነበሩብንን ከፍተቶች ይዘን አንቀጥልም፡፡ ያስፈረምናቸው ተጫዋቾች ምርጥ በመሆናቸው ቀስ በቀስ ቡድናችን ጥሩ ይሆናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡

አዳዲሶቹ የኤሌክትሪክ ፈራሚዎች ዋለልኝ ገብሬ እና ብሩክ አየለ በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ሲሆን ከአምናው የዞረ ቅጣት ያለበት ተከላካዩ በረከት ተሰማ አይሰለፍም፡፡

እውነታዎች

ተገናኙ – 20

ኤሌክትሪክ አሸነፈ – 9

አቻ – 9

መከላከያ አሸነፈ – 2

ኤሌክትሪክ አስቆጠረ – 32

መከላከያ አስቆጠረ – 20

 

ያጋሩ