የዓብስራ ተስፋዬ ድንቅ ግብ ለደደቢት የዓመቱን የመጀመርያ ሶስት ነጥብ አስጨብጣለች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ ከተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች መካከል መቐለ ላይ በደደቢት እና ወላይታ ድቻ መካከል የተደረገው ጨዋታ በሰማያዊዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ለደደቢት በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሶሰት ነጥብ ሆኖ ተመዝግቧል።

ደደቢት ከባለፈው ሳምንት ስብስቡ ኩማ ደምሴን በአለምዓንተ ካሳ፣ አሌክሳንደር ዓወትን በአብርሃም ታምራት ቀይሮ ሲያስገባ በእንግዳው ወላይታ ድቻ በኩል ባለፈው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ አቻ ከተለያየው ስብስቡ እሸቱ መናን በዐወል አብደላ፣ ባዬ ገዛኸኝን በአንዱዓለም ንጉሴ፣ ኄኖክ ኢሳይያስን በያሬድ ዳዊት፣ ኄኖክ አርፊጮን አብዱልሰመድ ዓሊ ተክተው ገብተዋል።

በደደቢቶች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በርከት ያሉ የግብ እድሎች ተፈጥረዋል። በተለይም ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በርከት ያሉ እድሎች ሲፈጥሩ አክዌር ቻም ከርቀት መቷት ለጥቂት የወጣችው የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ እና መድሃኔ ብርሃኔ በጥሩ ሁኔታ አታሎ ገብቶ አክርሮ መቷት ታሪክ ጌትነት የመለሳት ኳስ በደደቢቶች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

በጨዋታው የመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው እና በዋነኝነት ለብቸኛ አጥቂው አንዱዓለም ንጉሴ በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩት ወላይታ ድቻዎች  በመረጡት አጨዋወት ንፁህ የግብ እድል ባይፈጥሩም በሁለት አጋጣሚዎች መሪ መሆን የሚችሉበት ዕድል ፈጥረው ነበር። በተለይም ፍፁም ተፈሪ ከርቀት አክርሮ መቶ ረሺድ ማታውሲ ያዳነው እና አብዱልሰመድ ዓሊ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ደደቢቶች በአለምዓንተ ካሳ፣ እንዳለ ከበደ እና መድሃኔ ብርሃኔ የጎል እድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም እንዳለ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዙ ያደረጋት ሙከራ ደደቢትን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ከመጀመርያው የተሻለ የኳስ ፍሰት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ብዙ ንፁህ የግብ እድሎች አልታዩበትም። በመጀመርያው አጋማሽ በደደቢት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ወላይታ ድቻዎች በዚህ ክፍለ ጊዜ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾቻቸው ይበልጥ ተጠጋግተው እና ወደ መሃየሀል ሜዳ ጠበው እንዲጫወቱ በማድረጋቸው የተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተወሰነ መልኩ ቢመልሱም ለአንዱዓለም ንጉሴ በረጅሙ ከሚሻገሩት ኳሶች ውጪ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው የግብ ዕድል አልፈጠሩም። በአንፃሩ ደደቢቶች ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ ወደ ቀጥተኛ አጨዋወት እና ዳግማዊ አባይ በተሰለፈበት ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለማጥቃት ጥረቶች አድርገዋል። በ52ኛው ደቂቃ ላይም አክዌር ቻም በረጅሙ የተላከችለት ኳስ አብርዶ አጠገቡ ለነበረው እና በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው የዓብስራ ተስፋዬ አቀብሎት የዓብስራ ከረጅም ርቀት ድንቅ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎችም እጅግ በርካታ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም እዮብ ዓለማየሁ ከቅጣት ምት የተሻገረችለት ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ እና አንዱዓለም ንጉሴ ተገልብጦ ያደረጋት ሙከራ በድቻ በኩል ከተፈጠሩት የግብ እድሎች ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ሙከራዎች ውጭም በ89ኛው ደቂቃ ሳምሶን ቆልቻ  ከግቡ ቅርብ ርቀት ያገኛትን ኳስ ጨርፎ ያደረጋት ሙከራ ድቻዎችን ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማስገኘት የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

ጨዋታው 1-0 መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢቶች በዓመቱ የመጀመርያ ሶስት ነጥብ ሲያሳኩ ወላይታ ድቻዎች በዚህ ዓመት ከሜዳቸው ውጭ ያላቸው ድል ያለማስመዝገብ መቀየር አልቻሉም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *