ሰአት – 11፡30
ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም
አምና 2ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ደደቢት በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመርያ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል፡፡ ከብሄራዊ ሊጉ ግማሽ ደርዘን የሚሆን ተጫዋች ያስፈረመውና አዲስ አሰልጣኝ የቀጠረው ደደቢት ነገ ይፈተናል፡፡
አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በብሄራዊ ቡድን የሚገኙ ተጫዋቾቻቸው መመለሳቸው ለቡድናቸው ጥንካሬ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
‹‹ ቡድኔ በጥሩ ሁኔታ እየተዋሃደ እና ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን የነበሩት ተጫዋቾች ቡድናችንን ሲቀላቀሉ ደግሞ የበለጠ ጥሩ እንሆናለን፡፡ ስዩም በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ የታሪክ ጌትነት መመለስም በግብ ጠባቂ ላይ ያለንን ክፍተት ይደፍንልናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ከደደቢት በኩል አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ ከጉዳቱ ባለማገገሙ አይሰለፍም፡፡ ተካልኝ ደጀኔ ከጉዳቱ ቢያገግምም ለነገው ጨዋታ መድረሱ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ወላይታ ድቻ እንደ ደደቢት ሁሉ ከብሄራዊ ሊጉ በርካታ ተጫዋች አስፈርሞ የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡ ብዙዎች ድቻ ባለው የተጫዋች ስብስብ የውድድር ዘመኑ ይከብደዋል ቢሉም አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ግን በቡድናቸው ተማነዋል፡፡
‹‹ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ጥሎ ማለፉ እና ሴንትራል ዋንጫ ጨዋታ ድረስ ለፕሪሚየር ሊጉ ይዘን የምንቀርበውን ቡድን ለመገምገም ችያለው፡፡ ከሴንትራል ዋንጫ ፍፃሜ በኋላ ባሉት ቀናት ደግሞ ጉድለቶቻችንን ለማረም ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡ የተሟላ ቡድን ይዘን ለመቅረብም ጥረት አድርገናል፡፡
‹‹ በቡድኔ ላይ እስካሁን እያየሁት ያለው ጥንካሬ አስደስቶኛል፡፡ ቡድናችን የተረጋጋ ሲሆን ተጫዋቾቼም የውድድር ዘመኑን በጥሩ አቋም ለመዝለቅ ተዘጋጅተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡
ከወላይታ ድቻ በኩል 5 ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት አይደርሱም፡፡ እንዳለ መለዮ ፣ አብዱልከሪም ጀማል ፣ ዳግም ንጉሴ ፣ ፀጋ አለማየሁ እና ስንታየሁ መንግስቱ ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የእርስ በእርስ ግንኙነቶች እውነታዎች
ተገናኙ – 4
ደደቢት አሸነፈ – 3
አቻ – 0
ወላይታ ድቻ አሸነፈ – 1
ደደቢት አስቆጠረ – 10
ወላይታ ድቻ አስቆጠረ – 5
-ደደቢት አዲስ አበባ ላይ ድቻን ባስተናገዳቸው 2 ጨዋታዎች 7 ግቦች አስቆጥሯል፡፡
-ደደቢትን ለቆ ወደ ወላይታ ድቻ ያመራው ሰለሞን ሐብቴ ለመጀመርያ ጊዜ ደደቢትን ይገጥማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
-ደደቢት አምና በመክፈቻ ጨዋታ ወልድያን 6-1 ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ በዳሽን ቢራ በሜዳው 1-0 መሸነፉ ይታወሳል፡፡