የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅድመ ውድድር ዘመን ዳሰሳ (ክፍል 2)

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን ዛሬ ይጀመራል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ትላንት ባለፈው የውድድር ዘመን ከ1-7 የወጡ ክለቦችን በአጭሩ መዳሰሷ የሚታወስነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ከ8ኛ ጀምሮ ያጠናቀቁትን እና አዲስ ያደጉትን ቡድኖች ለማስቃኘት ትሞክራለች፡፡

Defense_Force_SC_logo8.መከላከያ

ያለፈው አመት ደረጃ – 8ኛ

ወሳኝ ግዢዎች – ባዬ ገዛኸኝ እና አዲሱ ተስፋዬ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – የለም

የውድድር ዘመኑን በኢትዮጵያ ዋንጫ ድል የጀመረው መከላከያ በአፍሪካ ውድድር ከመሳተፍ አልፎ በፕሪሚየር ሊጉ ከአምናው የተሻለ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በማለም የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡

ጠንካራ ጎን

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከመልሶ ግንባታ ይልቅ ተጨማሪ ተጫዋች በማስፈረም ላይ በማተኮራቸው የተረጋጋ የቡድን ስብስብ ይዘዋል፡፡ 2008 ከገባ በኋላ ኬሎች ቡድኖች በተሻለ በርካታ የነጥብ ጨዋታ በማድረጋቸውም መከላከያ የተሻለ የውድድር መንፈስ ይዞ ፕሪሚየር ሊጉን ይጀምራል፡፡

መከላከያ ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ከፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች የላቀ ነው፡፡ ቡድኑ የሚይዘውን ኳስ ወደ ግብ እድልነት መለወጥ ላይ ድክመት የነበረበት ቢሆንም ዘንድሮ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ይህንን ድክመት ያሻሻለ አስመስሎታል፡፡ በተለይ መሃመድ ናስር ከጉዳት መልስ ግብ የማስቆጠር ብቃቱ ድንቅ ሆኗል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ ወደ ግብ ማስቆጠር ብቃቱ ከተመለሰ የመከላከያ የማጥቃት ኃይል አስፈሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ያሉት አጥቂዎች ባህርይ የተለያየ መሆንም አሰልጣኙን ይጠቅማል፡፡

ደካማ ጎን

አምና በድንገት በሞት ያጡትን ድንቅ አማካይ ተክለወልድ ፍቃዱን ክፍተት በሚገባ አልሸፈኑም፡፡ በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ የተክለወልድን ኳስ የማሰራጨት ግባርን ሲፈፅም ቢስተዋልም በአሰልጣኙ እምነት ያገኘ አይመስልም፡፡ የክረምቱ ግዢ ያተኮረውም በአጥቂ እና ተከላካይ መስመር ተጫዋች ላይ በመሆኑ የቡድኑ ጠንካራ ጎን የሆነው የአማካይ ክፍል ላይ አዲስ ኃይል እንዳንመለከት አድርጎናል፡፡

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ጀማል ጣሰው (ይድነቃቸው ኪዳኔ)

ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – ቴዎድሮስ በቀለ (ሚልዮን በየነ) – ነጂብ ሳኒ

ምንይሉ ወንድሙ – በኃይሉ ግርማ – ሚካኤል ደስታ – ፍሬው ሰለሞን

ባዬ ገዛኸኝ (ሙሉአለም ጥላሁን)- መሃመድ ናስር

Wolaitta Dicha9. ወላይታ ድቻ

የአምና ደረጃ – 9ኛ

ወሳኝ ግዢዎች – ቶማስ ስምረቱ ፣ አማኑኤል ተሾመ እና ቴዎድሮስ መንገሻ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – ባዬ ገዛኸኝ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ አሸናፊ ሽብሩ እና አዲሱ ተስፋዬ

አዲሱ የውድድር ዘመን አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ከሚችሉ ቡድኖች አንዱ ወላይታ ድቻ ነው፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ ያለፉትን 2 አመታት የክለቡ ወሳኝ ተጫዋቾች የነበሩት ተጫዋቾች በመልቀቃቸው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድናቸውን እንደአዲስ እንዲገነቡ አስገድዷቸዋል፡፡

ጠንካራ ጎን

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በክለቡ መቆየታቸው ለድቻ መልካም ዜና ነው፡፡ ቡድኑን የሚያነሳሱበት እና ሜዳ ላይ የታጋይነት መንፈስ እንዲኖራቸው የሚጠቀሙበት መንገድ ሙገሳ የሚቸረው ነው፡፡ ቡድኑ በሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫ ላይ 3ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቀስ በቀስ ከቡድኑ የሚፈልጉትን ታታሪነት እያገኙ ይመስላል፡፡

የክለቡ ደጋፊዎች ለቡድኑ ውጤታማነት ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ ቡድኑ በአዲስ አበባ ደጋፊ ከሌላቸው ክለቦች ጋር ሲጫወት በሜዳው የመጫወት ያህል እንዲሰማው ያደርጋሉ፡፡

ደካማ ጎን

ከወንድወሰን አሸናፊ እና ሰለሞን ሀብቴ በቀር በክረምቱ የፈረሙት ተጫዋቾች የተገኙት ከብሄራዊ ሊግ ክለቦች ነው፡፡ ምንም እንኳን ወላይታ ድቻ ያለፉትን 2 አመታት በሊጉ ወገብ ላይ ያጠናቀቀው እውቅና ባልነበራቸው ተጫዋቾች ተጠቅሞ ቢሆንም በክረምቱ እንቅስቃሴው ከሰንጠረዡ ወገብ በላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ስራ ሰርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

አስራት ሚሻሞ (ወንድወሰን አሸናፊ)

ሙባረክ ሽኩሪ – ተክሉ ታፈሰ – ቶማስ ስምረቱ

አናጋው ባደግ – ዮሴፍ ዴንጊቶ – አማኑኤል ተሾመ – ኃይለየሱስ ብርሃኑ – ሰለሞን ሀብቴ

ቴዎድሮስ መንገሻ (እንዳለ መለዮ) – አላዛር ፋሲካ

Hawassa Kenema

10. ሀዋሳ ከነማ

ያለፈው አመት ደረጃ – 10ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – አስቻለው ግርማ ፣ ኃይማኖት ወርቁ እና በረከት ይስሃቅ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – የለም

 

ሀዋሳ ከነማ ከአምናው መጥፎ የውድድር ዘመን በኋላ ዘንድሮ ጠንካራ እና የተረጋጋ ስብስብ ይዞ ፕሪሚየር ሊጉን ይጀምራል፡፡ በወረቀት ላይ የተሟላ የሚመስለውና የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ውበቱ አባተን የያዘው ሀዋሳ ከነማን ለቻምፒዮንነት ፉክክር ማጨት ስህተት አይሆንም፡፡

ጠንካራ ጎን

ሀዋሳ ከነማ በስብስብ ደረጃ ሊበለጥ የሚችለው ምናልባትም በቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው፡፡ በየቦታው ምርጥ ተጫዋቾችን ከመያዙ በተጨማሪ በክረምቱ እምብዛም ለውጥ ያላስተናገደ ቡድን በመሆኑ በተረጋጋ ስብስብ ፕሪሚየር ሊጉን ይጀምራል፡፡ አምና ከግማሽ የውድድር ዘመን ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ቡድናቸውን በሚፈልጉት መልኩ ለማዘጋጀት በቂ ጊዜ አግኝተዋል፡፡

የሀዋሳ ከነማ የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾች ለየትኛውም ቡድን ተከላካይ ፈተና የመሆን አቅም ያለው ነው፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ በአማራጮች የተሞላ የማጥቃት ባህርይ ያላቸውን ተጫዋቾች ይዟል፡፡

ደካማ ጎን

ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ እንደታየው በኳስ ቁጥጥር የበላይ ቢሆንም በማጥቃት ዞን ላይ ደካማ ነው፡፡ ለዚህም አሰልጣኙ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት እና በብሄራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት በበቂ ሁኔታ አለመሟላታቸውን እንደምክንያት አስቀምጠዋል፡፡ በማጥቃት ወረዳው ያለውን ብቃት ካሻሻለ ሀዋሳ ከነማ መልካም የውድድር ዘመን ማሳለፉ አይቀሬ ነው፡፡

 

ግምታዊ አሰላለፍ

ብሪያን ቶቤጎ

ግሩም አሰፋ – ሙጂብ ቃሲም – ግርማ በቀለ – ተስፋ ኤልያስ (አዲስአለም ተስፋዬ)

ኃይማኖት ወርቁ – ሙሉጌታ ምህረት

ጋዲሳ መብራቴ – ታፈሰ ሰለሞን – አስቻለው ግርማ

በረከት ይስሃቅ (ተመስገን ተክሌ)

electric 11. ኤሌክትሪክ

ያለፈው አመት ደረጃ – 11ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – አሸናፊ ሽብሩ እና ብሩክ አየለ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – ራምኬል ሎክ እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን

አምና ከመውረድ በመጨረሻው ጨዋታ የተረፈው ኤሌክትሪክ በርካታ ተጫዋቾች ከማስፈረሙ በቀር በቡድኑ ላይ የለውጥ አየር እየነፈሰ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት ላለመውረድ የተጫወተው ቡድን ዘንድሮም ሊቸገር እንደሚችል በአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ አሳይቶናል፡፡

ጠንካራ ጎን

የኤሌክትሪክ በንፅፅር ጠንካራ ጎን ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው የተከላካይ መስመሩ ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በቦታው በርካታ ተጫዋቾች ቢፈራረቁም የተከላካይ ክፍሉ ከሌሎች ክፍሎች የተሻለ ነበር፡፡

ደካማ ጎን

ኤሌክትሪክ ለክለቡ የሚመጥን አሰልጣኝ አልያዘም፡፡ ብርሃኑ ባዩ በክለቡ ለረጅም ጊዜ የቆዩት በረዳት አሰልጣኝነት ሲሆን ባለፈው የውድድር ዘመን አጋማሽ ዋና አሰልጣኝ ከሆኑ ወዲህ ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላሳዩም፡፡

የማጥቃት አጨዋወቱ ምናልባትም በሊጉ ደካማው ነው፡፡ ቡድኑ ፈጠራ የማይታይበት ከመሆኑ በተጨማሪ ቋሚ ግብ አስቆጣሪ የለውም፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

አሰግድ አክሊሉ

አወት ገ/ሚካኤል – በረከት ተሰማ – ሲሴ ሃሰን – አለምነህ ግርማ

ብሩክ አየለ – አሸናፊ ሽብሩ – አዲስ ነጋሽ – አሳልፈው መኮንን

ማናዬ ፋንቱ – ፒተር ኑዋድኬ

dashen 12. ዳሽን ቢራ

ያለፈው አመት ደረጃ – 12ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – ያሬድ ባዬ እና ተክሉ ተስፋዬ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – የለም

ያለፉትን 2 አመታት በፕሪሚየር ሊጉ የሚጠበቅበትን ያህል ያልሆነው ዳሽን ቢራ ዘንድሮ ጠንክሮ የመጣ ይመስላል፡፡ የአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ ቻምፒዮን የሆኑት ዳሽኖች ዘንድሮ ከሁለቱ አመታት የተሻለ ደረጃ ይዘው ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጠንካራ ጎን

የዳሽን ቢራ ጠንካራ ጎን የተከላይ ክፍሉ ነው፡፡ ቡድኑ በማጥቃት ላይ እንዳለበት ድክመት ቢሆን ኖሮ በመጣበት አመት ወደ ብሄራዊ ሊግ ይወርድ ነበር፡፡ በ2006 በሊጉ ጥቂት ግብ ያስተናገደ ቡድን የነበረው ዳሽን አምና 32 ግቦች አስተናግዶ 12ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ በክረምቱ በአንጋፋው አይናለም ኃይለ ምትክ የአውስኮዱን ያሬድ ባዬ ማምጣታቸው የተከላካይ ክፍሉ ዳግም እንዲጠናከር አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዲሱ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ በአካል ብቃት ላይ የተመሰረተ እና መከላከልን የሚወድ ቡድን መስራት ይመርጣሉ፡፡

ቡድኑ ከቆሙ እና ተሸጋሪ ኳሶች ግብ በማስቆጠር የተካነ እንደሆነ በአምበር ዋንጫ ላይ አሳይቷል፡፡

አምና በመጀመርያው ዙር የየተሻ ግዛው ግቦች ጥገኛ የነበረው ዳሽን አጥቂው ኤዶም ሆሶውሮቪን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ወደ ቡድኑ ከቀላቀለ ወዲህ ቋሚ ግብ አስቆጣሪ አግኝቷል፡፡

 

ደካማ ጎን

የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት አሁንም አልተሻሻለም፡፡ ከረጃጅም ኳሶች ውጪ ቡድኑ በተደራጀ ሁኔታ የግብ እድል ሲፈጥር አይታይም፡፡ የማጥቃት አማካዮች በበቂ ሁኔታ የሌለው ቡድን በመሆኑ አጥቂዎች ከአማካዮች ተቆርጠው ይታያሉ፡፡

ዳሽን ቢራ በንፅፅር ከሌሎች የበለጠ ጉዞ ያደርጋል፡፡ ይህ ቡድኑን ያዳክመዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ደረጄ አለሙ (ቢንያም ሃብታሙ)

ያሬድ ዘውድነህ – ያሬድ ባዬ – አለማየሁ ተሰማ – አምሳሉ ጥላሁን

ሳሙኤል አለባቸው – አስራት መገርሳ – ምንያህል ይመር

የተሻ ግዛው (ኤርሚያስ ኃይሉ) – መስፍን ኪዳኔ – ተክሉ ተስፋዬ

ኤዶም ሆውሶሮቪ

Diredawa

13 ድሬዳዋ ከነማ

ያለፈው አመት ደረጃ – የብሄራዊ ሊግ ቻምፒዮን

ቁልፍ ግዢዎች – ሳምሶን አሰፋ እና ሲሳይ ደምሴ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – የሉም

ድሬዳዋ በ2004 ወደ ብሄራዊ ሊግ ከወረደ በኋላ ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አድጓል፡፡ በብቸኛዋ ሴት አሰልጣኝ እየተመራም የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡ ከብሄራዊ ሊጉ ድል ማግስት የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በመቀላቀሉ ድሬዳዋ ለሊጉ ፈተና ራሱን አዘጋጅቷል፡፡

ጠንካራ ጎን

ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ሰብስቦ ከነባሮቹ ጋር አጣምሯል፡፡ በተለይም በተከላካይ መስመር ላይ የሲሳይ ፣ ፍሬው ብርሃን እና ተስፋዬ ዲባባ መኖር ቡድኑን ይጠቅመዋል፡፡

በሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫ ላይ ድረዳዋ አማካይ ክፍሉም ጠንካራ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ በአካል ብቃት የዳበሩ እና የቴክኒክ ክህሎት ያቸውን አጣምሮ ይዟል፡፡

ደካማ ጎን

ቡድኑ በወረቀት ላይ ለሊጉ የሚመጥን ስብስብ ቢይዝም አብዛኛዎቹ ተሰላፊዎች የፕሪሚየር ሊግ ልምድ የላቸውም፡፡ በዞን የተከፈለ በተከፈለ ውድድር ወደ መጨረሻው ዙር ያለፉትና የማጠቃለያውን ውድድር በሜዳቸው የተጫወቱት ድሬዳዋ ከነማዎች ዘንድሮ ረጃጅም ጉዞዎች ለማድረግ ይገደዳሉ፡፡ እስከ ነሃሴ አጋማሽ ድረስ በነጥብ ጨዋታዎች በመዝለቃለቸው የውድድሩ ፎርማት ሊያዳክማቸው ይችላል፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ሳምሶን አሰፋ

ሲሳይ ደምሴ (አቤል ፀጋዬ) – ተስፋዬ ዲባባ – ሽመልስ አበበ (ሲሳይ ደምሴ) – ፍሬው ብርሃን

ይሁን እንዳሻው – በድሩ ኑርሁሴን – ዮናስ ገረመው

ሱራፌል ዳንኤል – ፍቃዱ ወርቁ (አቅሌስያ ግርማ) – በላይ አባይነህ

Copy of Hosaena

14. ሀዲያ ሆሳእና

ያለፈው አመት ደረጃ – ብሄራዊ ሊግ 2ኛ

ቁልፍ ግዢዎች – ጃክሰን ፊጣ

ያጧቸው ወሳኝ ተጫዋቾች – ቴዎድሮስ መንገሻ

ሀዲያ ሆሳእና ለመጀመርያ ጊዜ በፕሪሚየር ሊጉ ይሳተፋል፡፡ ሳይጠበቅ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ሆሳእና ቡድኑ ላይ ለውጥ ሳያደርግ የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከብሄራዊ ሊግ ይዞት የመጣው እንደነ ወላይታ ድቻ ተፎካካሪ ሆኖ መቆየት እንደሚችል አልያም እንደነ ወልድያ እና ውሃ ስፖርት በመጣበት አመት ደካማ አቋም እንደሚያሳይ ለመመልከት ጊዜው ደርሷል፡፡

ጠንካራ ጎን

ሀዲያ ሆሳእና በብሄራዊ ሊጉ በማጥቃት አጨዋወታቸው ከተወደሱ ቡድኖች አንዱ ነው፡፡ በዱላ ሙላቱ ፣ ቴድሮስ መንገሻ እና ተዘራ አቡቴ የሚመራው የማጥቃት አጨዋወት የውድድሩ ድምቀት ነበር፡፡

ከቴዎድሮስ መልቀቅ በቀር ሌሎቹ ተጫዋቾች በቡድኑ በመቆየታቸው የተዋሃደ ቡድን ልንመለከት እችላለን፡፡ አሰልጣኝ ግርማ ከቡድኑ ጋር ለረጅም ጊዜ በመቆየታቸውና ተጫዋቾቹም ከአሰልጣኙ ጋር አብረው በመቆየታቸው ተግባብተው ለመስራት አይቸገሩም፡፡

ደካማ ጎን

ቡድኑ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ የለውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ድሬዳዋ ከነማ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን አልሰበሰበም፡፡ አምና በወልዲያ ላይ የተከሰተው ዘንድሮ በሆሳእና ሊከሰት ይችላል፡፡

ሆሳእና ብዙዎች በማጠቃለያው ውድድር ላይ የተሰራ ቡድን እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ለፕሪሚየር ሊጉ ያለፈውም ሳይጠበቅ ነው፡፡ ይህም ተዟዙሮ መጫወትን በሚጠይቀው ፈታኙ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ሊቸገር ይችላል ተብሎለታል፡፡

 

ግምታዊ ቋሚ አሰላለፍ

ሀብቴ ከድር (ጃክሰን ፊጣ)

ንጋቱ ዳሬ – ታረቀኝ ጥበቡ – ሄኖክ አርፊጮ – ውብሸት አለማየሁ

አየለ ተስፋዬ – አበው ታምሩ – ሀብቶም ገ/እግዚአብሄር – ዱላ ሙላቱ

ተዘራ አቡቴ – ማቴዎስ ብርሃኑ

 

ያጋሩ