የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ባደረገው ስብሰባ የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ አስተናጋጅነት እንዲካሄድ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በ24 ሃገራት መሃከል በሰኔ ወር ላይ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ውድድር አዘጋጅነት በቅድሚያ ለካሜሩን ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር በዝግጅት እና በመሠረተ ልማት ጥራት ችግር ምክኒያት ዕድሉን ልትነጠቅ ችላለች። ካሜሩንን በመተካት ውድድሩን ለማስተናገድም ግብፅ፣ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ፍላጎት አሳይተው ነበር። የሞሮኮ እግርኳስ ማህበር ከሌላ የአረብ ሃገር ጋር ውድድር ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው በመግለፅ ከፉክክሩ ራሱን በማግለሉም የአስተናጋጅነቱ እጣ ለግብፅ ወይም ደቡብ አፍሪካ እንደሚደርስ ታውቆ ቆይቷል።
የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ምርጫም ከ18 ድምፅ ውስጥ ግብፅ 16ቱን በመውሰድ የአስተናጋጅነቱን ፉክክር ማሸነፍ ስትችል ደቡብ አፍሪካ አንድ ድምፅ ብቻ አግኝታለች፤ አንድ ድምፀ-ተአቅቦ ተመዝግቧል። ማዳጋስካራዊው የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት አህመድ አህመድም ከምርጫው ክንውን በኋላ የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ አስተናጋጅነት እንደሚደረግ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ ግብፅ የአፍሪካ ዋንጫውን የማስተናገድ ዕድል በታሪኳ ለአምስተኛ ጊዜ ከ2006 በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝታለች። በአህጉራችን በእግርኳስ መሠረተ ልማቱ በኩል ከማይታሙ ሃገራት አንዷ የሆነችው ግብፅ ለመስተንግዶው የሚኖራት የዝግጅት ጊዜ አጭር ቢሆንም ያለምንም እንከን ውድድሩን ለማዘጋጀት በቁርጠኝነት እንደምትሰራ እና የግብፅ መንግስትም ለዚህ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዳሳየ ከእግርኳስ ማህበሩ የተሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኬንያ፣ ጋና እና ሴራሊዮን ጋር ተደልድሎ ጨዋታዎችን ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሴራሊዮን በፊፋ መቀጣቷን ተከትሎ ከወዲሁ የማጣሪያ ጉዞውን ያጠናቀቀ ሲሆን በአንድ ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ በመያዝ በውድድሩ እንደማይሳተፍ እንዳረጋገጠ ይታወቃል።