የግል አስተያየት | ባለ አምስት ኮከቡ አዳማ ከተማ… ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች

አስተያየት በዘርዓይ ኢያሱ

የ2011 ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጣው አዳማ ከተማ ከመከላከያ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 5ለ1 አሸንፎ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡ እርግጥ ከመከላከያ በኩል ተመስገን ገብረ ኪዳንና ዓለምነህ ግርማ በቀይ ካርድ መውጣታቸው አዳማ በሰፊ የግብ ልዩነት ለማሸነፉ ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ ነገር ግን የዕለቱ የአዳማ ከተማ አጀማመር ምርጥ የነበረ ከመሆኑ ባሻገር ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን ችሎ ነበር፡፡ እንዲሁም ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ደጋግሞ መሄድ መቻሉ ከግምት ሲገባ ደግሞ የአዳማን የእለቱን አጀማመር አለማድነቅ አስቸጋሪ ነው፡፡

ቡድኑ ብዙ ጠንካራ ጎኖች እንደነበሩት ሁሉ ለምን ብለን እንድንጠይቅ ያስገደዱን መጠነኛ ክፍተቶችንም ተመልክተናል፡፡ ለመሆኑ የቡድኑ ጥንካሬና ደካማ ጎን ምን ነበር? እንደሚከተለው እናየዋለን፡፡

አጀማመር

አምና በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው አዳማ ከተማ የዘንድሮው ጅማሮው ጥሩ አልነበረም፡፡ የመጀመሪውን ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር በሜዳው 2ለ0 የተሸነፈበት ጨምሮ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፡፡ በቡድኑ ቁመና ያልተደሰቱ አንዳንድ ደጋፊዎች የማስተካከያ እርምጃዎች ይወስዱ ዘንድ ሲጠይቁ እንደነበር በማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ አንበብናል፡፡

ይሁን እንጂ በስድስተኛው ሳምንት መርሐ ግብር መቀሌ 70 እንደርታን በሜዳው ገጥሞ 3ለ1 ያሸነፈበትን ጨዋታ ጨምሮ ከአራት ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ቡና ብቻ ተሸንፎ ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች በድል በማጠናቀቅ ዘጠኝ ነጥብ በመሰብሰብ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፡፡ በስምንት ጨዋታዎች ያገኘነውም የነጥብ ብዛት 11 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ የነጥብ ብዛትና  የጠቀመጠበት የደረጃ ሰንጠረዥ ቢያንስ የቡድኑን በራስ መተማመን ከፍ ከማድረግ አኳያ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ባለሁለት መልክ ቡድን…

ባለፈው የውድድር ዓመት አዳማ ከተማ ለዋንጫ ሲፎካከር ወጣቶቹ  ልምድ ካለቸው ተጨዋች ጋር የነበራው ጥምረት ድንቅ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሱራፌል ዳኛቸው ክለቡን ቢለቅም እንደ እነ ከነዓን ማርክነህና፤ በረከት ደስታና ቡልቻ ሹራ ያሉ ወጣቶች አሁንም ቡድኑን የተሻለ ርቀት ሊያራምዱት እንደሚችል ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ያስተዋልኩ ነገር ቢኖር ስብስቡ ሁለት መልክ ያለው ሆኖ የሜዳ ላይ አሰፋፈራቸውም የተለየ መሆኑን ነው፡፡ ቀደም ሲል ከላይ  እንደጠቀስኩት ቡድኑ በወጣትና በሊጉ ረጅም ዓመት በተጫወቱ ተጨዋቾች የተደራጀ ነው፡፡ አሰፋራቸውም እንደ እደሜ ደረጃቸው የተከፈለ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ተከላከዮቹንና የሁለቱን የአማካይ ተከላካዮች አሰፋር ካስተዋልን ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡

በተከላካይ ስፍራ ቴዎድሮስ በቀለ፤ ተስፋዬ በቀለና ምኞት ደበበ እንዲሁም በአማካይ ተከላካይ ቦታ ደግሞ አዲስ ህንፃና ሳንጋሪ ተሰማርተዋል፡፡ ከእነዚህ ተጨዋች ፊት ለፊት ደግሞ ሮጠው ያልጠገቡና በቴክኒክ ብቃታቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ከነዓን ማርክነህ፤ በረከት ደስታና ቡልቻ ሹራ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ስምሪት ውስጥ የምናየው አስደናቂ ነገር ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች የመከላከል ቀጠናውን በካበተው ልምዳቸው ሲቆጣጠሩ ወጣትነታቸው እንደፈለጉ የሚያስሮጣቸው ወጣት ተጨዋችች ደግሞ የተጋጣሚያቸውን ተከላካይ ክፍል በቴክኒክ ክህሎታቸው ታግዘው የማሸበር ስራ ይሰራሉ፡፡ ታዲያ ልምድና ወጣትነት ሲጣመሩ እጅግ የተዋጣለትን አዳማ ከተማ የምናይበት ግዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ የዚህንም ተስፋ መከላከያን 5ለ1 ባሸነፉበት ጨዋታ ተመልክተናል፡፡

4-2-3-1 እና 5ለ1

የመከላከያው ጨዋታ አዳማ ከተማ ምን ቅርፅ እንዳለው ያሳየ እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ በዚህ ጨዋታ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም 4-2-3-1 ፎርሜሽን የጨዋታው ምርጫው ነበር፡፡ በዚህ አሰላለፍ የአማካይ አጥቂዎች ( የከነዓን፤ የቡልቻና የበረከት) የመከላካል ሽግግር ሲታከልበት የአማካዮቹ ቁጥር አምስት ይደርሳል፡፡ ይህ ደግሞ በ4-4-2 ዳይመንድ ይጫወት የነበረው ቡድን የስዩም ከበደ ቡድን  የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዳወስድ አድርጎታል፡፡ ይህ ማለት አዳማ ከተማ በአቀደው መሰረት እንዲጫወት አስችሎታል፡፡ በተለይደ ደግሞ ቡልቻ ሹራ፤ ከነዓን ማርክነህና በረከት ደስታ የተጋጣሚ ተከላካዮችን ተጭነው መጫወታቸው የመከላያ ተከላካዮችን ስራ ከማብዛቱ ባለፈ በአንፃሩ የአዳማ ተከላካዮች በእፎታ እንዲጫወቱ ረድቷቸዋል፡፡ በሌላ አገላለፅ ከፊት ለፊት ያሉት ተጨዋቾች የጠጋጣሚያቸውን ተከላካዮችና አማካዮች ተጭነው ይጫወቱ ስለነበር  ኳስ ወደ አዳማ ክልል የመሄድ እደሉ ጠባብ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የአዳማ ተከላካዮቹ ያለጫና እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል፡፡

ለዚህ ድል መገኘት  የሁሉም ተጨዋች ድርሻ ሳይዘነጋ የከነዓን ማርክነህ አስተዋፅኦ የጎላ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ከነዓን ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ከማቀበሉ ባሻገር የቡድኑን የማጥቃት አቅጣጫ ወደፊት በመውሰድ፤ የግብ እድሎችን በመፍጠርና የመከላካያው ቴዎድሮስ ታፈሰ ጨዋታ እንዳያደራጅ በመከላከሉ በኩል ድንቅ ስራ ሰርቷል፡፡ ስለሆነም በእለቱ ጨዋታ አራት ግቦችን ካስቆጠረው ዳዋ ሁጤሳ በተሻለ የጨዋታው ኮከብ እሱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በ4 ተከላካይ መጨረስ ለምን አስፈለገ…?

በሁለተኛው ግማሽ ተመስገን ገብረ ኪዳንና አለምነህ ግርማ በ54ኛውና በ59ኛው ደቂቃ በቀጥታ በቀይ ካርድ መውጣታቸውን ተከትሎ በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃም በኩል የታክቲክ ለውጥ ይደረጋል የሚል እምነት ነበር፡፡ ከመከላካያ ሁለት ተጨዋቾች በቀይ ካርድ እንደመውጣታቸው የተከላካይ ቁጥር ቀንሶ የአማካይ ወይም የአጥቂ ቁጥር በመጨመር የማጥቃ ሃይሉን ይበልጥ አጠናክሮ ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር በቻለ ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኑ ጨዋታውን በአራት ተከላካዮች በማሰማራት እንደጀመረ በዚያው ጨርሷል፡፡

በርግጥ ቡድኑ አምስት ጎሎችን እንደማስቆጠሩ ተጨማሪ ግብ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር በግብ ልዩነት ከመውረድ ማምለጥ እንዲሁም  ሻምፒዮን መሆን የሚቻል መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም ምሳሌ መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ባለፈው የውድድር አመት ጅማ አባ ጅፋር የሊጉ ሻምፒዮን የሆነው በግብ ልዩነት ነው፡፡ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ያጣው በጅማ አባ ጅፋር በግብ ክፍያ ተበልጦ ነው፡፡

የፕሪምየር ሊጉ መስራች ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፈው የውድድር ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ የወረደው በወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ በግብ ክፍያ ተበልጦ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የተሻለ ግቦችን ሰብስቦ ስለነበር ከመውረድ አምልጧል፡፡ ይህ እውነታ የሚያሳየን አሁን ላይ ያልተሰበሰበ የግብ ብዛት በዓመቱ መጨረሻ ለከፍተኛ ሃዘን የሚዳርግ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው አዳማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የስልት ለውጥ ለምን አላደረገም ስል የጠየኩት፡፡ አሰልጣኝ ሲሳይ አብራሃም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች ሲቀሩት ሁለት ተጨዋቾችን ቀይሮ አስገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ ታክታዊ ለውጥ ሳይሆን የደከመውን በደከመው መቀየር አልያም እድል ላላጉኙ እድል መስጠት ነው፡፡ ስለሆነም የተሻለ ውጤት ላመስመዝገብ በታክቲኩ በኩል ተለዋዋጭ መሆን በአጣም አስፈላጊ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ማጠቃለያ

በጥቅሉ አዳማ ከተማ ሜዳ ውስጥ የነበረው እንቅስቃሴ መልካም እንደነበር እንዲሁም ከከተማዋ አብራክ የተገኙ ወጣት ተጨዋች ለቡድኑ እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ ምን እንደሚመስል በደንብ የተመለከትንበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ታክታዊ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመመልከት ቢያንስ ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ጨዋታ ማየት አስፈላጊ ስለሚሆን ወደ ፊት አዳማ ከተማ የተመለከተ ጥልቅ ታክቲካዊ ትንታኔ የማዘጋጅ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ ለአሁን ግን እዚህ ላይ አበቃሁ…


*በአስተያየት ዓምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸኃፊውን እንጂ የድረ-ገጹን አቋም አይገልጹም፡፡

*ለጸኃፊው ያለዎትን አስተያየት በዚህ ኢሜይል አድራሻ መላክ ይችላሉ | zeray.eyassu@gmail.com


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *