ኤሌክትሪክ እና ደደቢት ፕሪሚየር ሊጉን በድል ከፈቱ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በይፋ በአዲስ አበባ ስታድየም ተጀምሯል፡፡ በመክፈቻው እለት በተደረጉ ጨዋታዎችም ደደቢት እና ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል፡፡

በ9፡00 መከላከያን የገጠመው ኤሌክትሪክ 1-0 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን በድል ከፍቷል፡፡ የኤሌክትሪክን የድል ግብ ናይጄርያዊው አጥቂ ፒተር ኑዋድኬ በ40ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡

በ11፡30 ደደቢት ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ደደቢት በ9ኛው ደቂቃ ሳምሶን ጥላሁን ባስቆጠረው የቅጣት ምት ግብ ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች በ61ኛው ደቂቃ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኃይለየሱስ ብርሃኑ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ ሆነዋል፡፡ የደደቢት የማሸነፍያ ግብ የተገኘችው በ80ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ሳኑሚ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አማካኝነት ነው፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ አንደኛ ሳምንት ቀሪ 5 ጨዋታዎች ነገ ይደረጋሉ፡፡ የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አዳማ አቅንቶ አዳማ ከነማን ይገጥማል፡፡ የአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ አሸናፊው ዳሽን ቢራ ዘንድሮ ያደገው ድሬዳዋ ከነማን ያስተናግዳል፡፡ በሲዳማ ደርቢ የሀዋሳ ሱንትራል ዋንጫ አሸናፊው ሀዋሳ ከነማ ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ አዲስ መጪው ሀዲያ ሆሳእና ደግሞ አርባምንጭን ይጎበኛል፡፡ ሁሉም ጨዋታዎች 9፡00 ላይ የሚጀምሩ ሲሆን 11፡30 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ የአንደኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ይሆናል፡፡

ያጋሩ