የኢትዮጵያ ዋንጫ | መከላከያ ጊዮርጊስን አሸንፎ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል

በኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተገናኙት መከላከያዎች በቴዎድሮስ ታፈሰ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለዋል። 

መከላከያ በአዳማ ከተማ በሰፊ የግብ ልዩነት ከተሸነፈበት የዘጠነኛ ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር አንፃር በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተው በነበሩት ዓለምነህ ግርማ እና ተመስገን ገብረኪዳን ምትክ አበበ ጥላሁን እና በኃይሉ ግርማን ሲተካ ፍሬው ሰለሞንም በምንይሉ ወንድሙ ምትክ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መጥቷል። በመጨረሻ የሊግ መርሀ ግብሩ ደቡብ ፖሊስን በጠባብ ውጤት ካሸነፈበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ኄኖክ አዱኛ ፣ አቤል ያለው እና ሳላሀዲን ሰይዲንን ተጠባባቂ በማድረግ በምትካቸው አብዱልከሪም መሀመድ ፣ አሜ መሐመድ እና ጌታነህ ከበደን አስጀምሯል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ኳስ መስርተው ለመጫወት ጥረት ያደርጉ የነበሩት መከላከያዎች የተጋጣሚያቸውን የአማካይ ክፍል አልፈው ወደ ሌላኛው የሜዳ አጋማሽ መድረስ ከብዷቸው ታይቷል። የምቋረጡት ቅብብሎቻቸውም መልሰው ራሳቸው ላይ አደጋ ሲፈጥሩ ይታይ ነበር። በመሆኑም ለፊት አጥቂያቸው ረዘም ያሉ ኳሶችን መጣልን እንደአማራጭ ወስደዋል። በዚህም 6ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት በረጅሙ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለለትን ኳስ ፍፁም በለዓለም አናት ላይ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት ግብጠባቂው በቀላሉ ይዞታል። ከዚህ ሙከራ ውጪ ግን አብዛኞቹ ረጃጅም ኳሶች በሚጣሉበት አጋጣሚ በሦስት የጊዮርጊስ ተከላካዮች መካከል ይታይ የነበረው ፍፁም ገብረማርያም በጊዮርጊስ የጨዋታ ውጪ መረብ ውስጥ እየገባ ኳሶቹ ውጤታማ አልሆኑም። 

መከላከያ ከሜዳው እምብዛም እንዳይወጣ ማድረግ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በበኃይሉ ፣ ታደለ እና አብዱልከሪም አማካይነት በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ለመግባት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ወደ መጨረሻ የግብ ዕድል ለመቀየር ግን ለኋላ መስመራቸው ጥሩ ሽፋን ይሰጡ የነበሩትን ተጋጣሚዎቻቸውን ማስከፈት አልቻሉም። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ከቆሙ ኳሶች የተሻሉ ዕድሎችን ሲፈጥር 27ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም መስፍን ከማዕዘን የተነሳን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ምንተስኖት ከበደ ከመስመር ላይ ሲያወጣበት በድጋሜ  ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ ወደ ግብ የላከው እና ይድነቃቸው ያዳነበት የተሻለው ሙከራ ነበር ። 

በሂደት መሀል ሜዳ ላይ የሚነጠቁ እና ያልተሳኩ ቅብብሎች እያታዩበት እንዲሁም ጉሽሚያዎች እየተበራከቱበት የሄደው ጨዋታ በጣሙን ተቀዛቅዞ ቆይቶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሙከራዎችን በማስተናገድ ነቃ ብሏል። በድንገየኛ ጥቃት ከጊዮርጊስ ተከላካይ መስመር ጀርባ መግባት እየተሳካላቸው የመጡት መከላከያዎች 40ኛው ደቂቃ ላይ የተገኟቸውን ሁለት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ፍፁም እና ቴዎድሮስ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። ቀስ በቀስ ተጋጣሚያቸውን ከኋላ ማስከፈት በቻሉት ጊዮርጊሶች በኩል ደግሞ 32ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ከታደለ የተቀበለውን ኳስ በግራ መስመር ይዞ በመግባት ሞክሮ ይድነቃቸው በቀላሉ የያዘበት እና 39ኛው ደቂቃ ላይም ራሱ አብዱልከሪም ከተቀማ ኳስ በዛው አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ አገባው ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራው ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረበት አጋጣሚም ተጠቃሽ ነው። ጊዮርጊሶች የዕረፍት ሰዓት በቀረበበት ጊዜም በሁለቱ አጥቂዎች ጌታነህ ከበደ እና አሜ መሀመድ ያደረጓቸው ሙከራዎች ለይድነቃቸው ኪዳኔ ከባድ ሆነው አልተገኙም።

ከዕረፍት መልስ መከላከያዎች ሁለት ቅያሪዎችን ሲያደርጉ ዳዊት እስጢፋኖስን በአጥቂው ፍቃዱ አለሙ በመተካት ወደ ቀደመው የ 4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፋቸው የመጡበት አግባብ መሀል ሜዳውን ክፍት አድርጎት ታይቷል። በመሆኑም ጨዋታው እንደተጀመረ ሁለቱም በድኖች በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ግብ የሚያደርሷቸውን ቅብብሎች ማድረግ ችለው ነበር። 52ኛው ደቂቃ ላይም መከላከያዎች ከአብዱልከሪም የነጠቁትን ኳስ ከሳሙኤል ታዬ የተቀበለው ፍፁም በግራ የጊዮርጊስ ሳጥን ጠርዝ ላይ አስቻለውን ለማለፍ ሲሞክር ጥፋት ተሰርቶበታል። በዚህም ምክንያት የተሰጠውን ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በድንቅ ሁኔታ በቀጥታ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከግቡ በኋላ በፍጥነት ወደ ጥቃት የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከማዕዘን ምት ከተነሳ እና ይድነቃቸው ከመለሰው ኳስ በሙሉዓለም አማካይነት ያደረጉት ሙከራ በተከላካዮች ጥረት ከግቡ መስመር ላይ የወጣ ነበር።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በሙሉ ኃይላቸው ወደ ማጥቃቱ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሀል ሜዳ ላይ የሚቀሟቸውን ኳሶች በሙሉዓለም መስፍን እና አቡበከር ሳኒ አማካይነት ወደ ሳጥን ውስጥ በመላክ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ከነዚህም ውስጥ 63ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ በቀኝ መስመር ገብቶ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ጊዮርጊሶች ተበራክተው ወደ ሳጥን ውስጥ በገቡበት አጋጣሚ አሜ ከቀኝ ወደ ግራ ያደረሰውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጋዲሳ መብራቴ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጊዮርጊሶች ሳላሀዲን ሰይድን ጭምር ወደ ሜዳ በማስገባት ከፊት ሶስት አጥቂዎችን ተጠቅመው አቻ ለመሆን ጥረታቸውን ቀጥለዋል።  71ኛው ደቂቃ ላይ ከበሀይሉ ግርማ የተቀማ ኳስ ሳጥን ውስጥ አቤል አሳልፎለት ሳላዲን ለጥቂት ከግቡ አፋፍ ላይ ያመከነው ኳስም ቡድኑን በውጤት ለማስተካከል የተቃረበ ነበር።

አማኑኤል ተሾመን ቀይረው በማስገባት አማካይ ክፍላቸውን በድጋሚ ወደ አምስት ከፍ ያደረጉት መከላከያዎች እስከጨዋታው ፍፃሜ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶች ቢበረክቱባቸውም በተለይም በመሀል ተከላካዩ አዲሱ ተስፋዬ ጥረት አብዛኞቹን ከግብ ክልላቸው አርቀዋል። መሀል ሜዳ ላይም ፍሬው እና ቴዎድሮስ የጊዮርጊስን ተጫዋቾችን ጫና ውስጥ በመክተት አልፎ አልፎ ወደ ፊት ቢሄዱም በአብዛኛው የጦሩ ተጫዋቾች በራሳቸው ሜዳ ላይ በመቆየት ንፁህ የግብ ዕድል እንዳይፈጠርባቸው በማድረግ ጨዋታውን 1-0 አሸናፊነት አጠናቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዋንጫ ውጤታማው ቡድን መከላከያ በሩብ ፍፃሜው ወደፊት በሚገለፅ ቀን የሚጫወቱት የመቐለ 70 እንደርታ እና ደቡብ ፖሊስን አሸናፊ ይገጥማል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *