ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተጫዋች ሊያሰናብት ነው

ኢትዮጵያ ቡና የውጭ ሀገር ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾቹ መካከል አንዱን የውል ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ሊያሰናብት መሆኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ የዝውውር ወቅት የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹን አማራጭ ለማስፋት በማሰብ በመጨረሻ የዝውውር ሰዓት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው የሆነው ላይቤሪያዊ አጥቂ ዴኮ ሾሌን ለሁለት ዓመት የውል ዘመን ማስፈረሙ ይታወሳል። ብዙ ተነግሮለት ቢመጣም እንደተጠበቀው መሆን ሳይችል በተጠባባቂ ወንበር ላይ አመዛኙን ጊዜ ያሳለፈው ሾሌ በሊጉ ቡድኑ ካደረገው ዘጠኝ ጨዋታ በሁለቱ ብቻ ተቀይሮ በመግባት በድምሩ ለ38 ደቂቃዎች ከመጫወት እና አንድ የማስጠንቀቂያ ካርድ ከመመልከት ባሻገር ተጽዕኖ መፍጠር ሳይችል ቀርቷል። አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስም ሆኑ የክለቡ አመራሮች በተጫዋቹ እንቅስቃሴ ደስተኛ ካለመሆናቸው የተነሳ በቅርቡ ውላቸውን በማፍረስ ሊያሰናብቱት እንደሆነ ከክለቡ አካባቢ  መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።

ለሀገሩ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ የመጫወት ዕድል ያገኘው እና በክለብ ህይወቱ  ለቱኒዚያው ቤዘርቲን ከ23 ዓመት በታች ቡድን የተጫወተው የመስመር አጥቂው ወደ ፈረንሳዩ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ቱር ለማምራት ሞክሮ ዝውውሩ ባለመሳካቱ ለሌላው የቱኒዚያ ክለብ ስታድ ጋቢሴን ሲጫወት ቆይቶ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው።

Leave a Reply