የኢትዮጵያ ዋንጫ | ፋሲል ከነማ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቅሏል

በኢትዮጵያ ዋንጫ አንደኛ ዙር በዛሬው ዕለት አንድ ጨዋታ መቐለ ላይ ተከናውኖ ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጪ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 1-0 በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል።

በጉዳት በርካታ ተጫዋቾቻቸው ያጡት ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ከእሁዱ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አብዱልዓዚዝ ኬይታ፣ ቢንያም ሲራጅ፣ እንየው ካሳሁን፣ ሪችሞንድ አዶንጎ፣ አፈወርርቅ ኃይሉ እና ብርሃኑ ቦጋለን አሳርፈው በበረከት አማረ፣ በረከት ተሰማ፣ ሮቤል አስራት፣ ሳምሶን ተካ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና አብዱልራህማን ፉሴይኒ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው ጀማል ጣሰው፣ ሰለሞን ሐብቴ፣ ሐብታሙ ተከስተ፣ አብዱልራህማን ሙባረክን በማሳረፍ በምትካቸው ሳማኬ ሚኬል፣ ፍፁም ከበደ፣ በዛብህ መለዮ እና ኤፍሬም ዓለሙ አካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።


የፋሲል ከነማ ሙሉ ብልጫ በታየበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት ተቸግረው ቢታዩም ፋሲሎች ተደጋጋሚ የግብ እድል ፈጥረዋል። በተለይ የመስመር ተጫዋቾቻቸው በዛብህ መለዩ እና ሽመክት ጉግሳን ቦታ ቀያይረው ሁለቱም የመስመር  ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ ተሳታፊ ካደረጉ በኋላ የተሻለ በመንቀሳቀስ እጅግ በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ሽመክት ጉግሳ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ስትሆን ሱራፌል ዳኛቸው አክርሮ መቷት በረከት አማረ ያዳናት እና ኤፍሬም ዓለሙ ከመስመር አሻምቷት ከግቡ ፊት ለፊት የነበረው በዛብህ መለዮ ያመከናት ኳሶችም የሚጠቀሱ ነበሩ።

በጨዋታው ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ በተጨማሪ የተሳካ የማጥቃት ሽግግር ያደረጉት ዐፄዎቹ በተጠቀሰው አጨዋወት እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር፤ ሰዒድ ሀሰን ከመስመር በጥሩ ሁኔታ ያሻማትን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ነፃ አቋቋም የነበረው በዛብህ መለዮ በግንባሩ ገጭቶ አልተጥቀመባትም እንጂ። ከዚ ውጭ በጨዋታው  ከቆሙ ኳሶች ጥሩ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ የታዩት ፋሲሎች በመጀመርያው አጋማሽ ማለቅያ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር ሽመክት ጉግሳ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ኤፍሬም አሻሞ ከግቡ መስመር የመለሳት ኳስም ከቆሙ ኳሶች ከተፈጠሩት ዕድሎች ትጠቀሳለች።


በመጀመርያው አጋማሽ በርካታ ተጫዋቾች ያለ ተፈጥሮአዊ ቦታቸው ያጫወቱት ቢጫ ለባሾቹ በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተው ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ቢንቀሳቀሱም ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ፤ በአንፃሩ ፋሲሎች በመጀመርያው ደቂቃ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ኢዙ ኢዙካ ከግቡ ፊት ለፊት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ መቶ በረከት አማረ ሲተፋት የተመለሰችው ኳስ ሽመክት ጉግሳ ቢመታትም በረከት አማረ በድጋሚ እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት አድኗታል። በ52ኛው ደቂቃ ደግሞ ሱራፍኤል ዳኛቸው ከመዓዘን ያሻማውን ኳስ ያሬድ ባየህ በግንባር ገጭቶ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ መነቃቃት ያሳዩት ወልዋሎዎች በሁለት አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም አብዱልራህማን ያሻማውን ኳስ ባልተለመደ ቦታ መሃል ላይ የተሰለፈው ተስፋየ ዲባባ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት ሙከራ ወልዋሎን አቻ ለማድረግ ከተቃረቡት ሙከራዎች የተሻለች ነበረች። ብርሃኑ አሻሞ ከቅጣት ምት መቷት ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ ያወጣት እና በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኤፍሬም አሻሞ እና ደስታ ደሙ በጥሩ ቅብብል ገብተው ያልተጠቀሙባት ኳሶችም ይጠቀሳሉ።


ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል ከመሄድ የጎንዮሽ ቅብብል የመረጡት ፋሲሎች በኤፍሬም ዓለሙ እና በዓለምብርሃን ይግዛው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው በዕለቱ ኮከብ ሆኖ የዋለው በረከት አማረ ግብ በመሆን ተርፈዋል። በተለይም የዓለምብርሃን ይግዛው ሙከራ የፋሲልን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ጨዋታው በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዐፄዎቹ ወደ ሩብ ፍፃሜ መሸጋገር የቻሉ ሲሆን የአዳማ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ አሸናፊንም በቀጣይ የሚገጥሙ ይሆናል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *