የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ 0-1 ፋሲል ከነማ

በኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ዛሬ መቐለ ላይ ፋሲል ከነማ ወልዋሎን 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ቡድናችን ፍቃደኛ ሆኖ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነው፤ እነሱ እኛን የተቀበሉበት መንገድ ደግሞ ሌላ ደስ የሚል አስተማሪ ነገር ነው” ውበቱ አባተ

ስለ ጨዋታው 

” ጨዋታው እንዳያችሁት ነው ወልዋሎ እንደባለፈ አልነበረም። ቢያንስ ባለፈው (እሁድ) በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ነበሩ። እንዳየሁት በርካታ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት ላይ ናቸው። ከዛ አንፃር የኛ ቡድን ብልጫ በመውሰድ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥሯል። ጥሎ ማለፍ አይመስልም፤ በኛ በኩል ጨዋታው በትኩረት ነው የተጫወትነው። እነሱም ያንን ይዘው ለመምጣት ፍላጎት እንደነበራቸው አይቻለው። ግን ብዙ ተጫዋቾች ጉዳት ላይ እንዳሉ ነው ያየሁት። ”

ስለ መቐለ ቆይታቸው

” ከመቀበል ጀምሮ የልምምድ ሜዳ በመስጠት፣ በሆቴል በቂ ምቾት እንዲሰማን በማድረግ፣ የልምምድ ሁኔታችን በአግባቡ በመከታተል ከኛ ጋር ነበር ህዝቡም ክለቡም። በጣም ደስ ይላል እንዲ አይነት ነገር፤  በሁሉም ክልሎች በሁሉም ክለቦች መዳበር እና መበረታታት አለበት። በቆይታችን በጣም ደስተኞች ነበርን።

ከህዝቡ የነበረን ድጋፍ ደስ ይላል፤ ይሄ ለሁላችን አስተማሪ ነው። ኳሱ በሰላም ተጫውተን የሃገራችን ኳስ በማሳደግ እንድናተኩር ይረዳናል። ”

ስለ ሁለቱ ክልል ክለቦች

” አብዛኛው ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ከእግር ኳስ ቤተሰቡ የዘለለ አይደለም። ወይ በደጋፊ ነው የሚነሳው ወይም በዳኛ፤ አለበለዛ በኛ አሰልጣኞች ነው የሚነሳው። እና ትግራይም መጣህ ሌላም ክልል ሂድ እግርኳስ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው። ህጉ የሚፈቅደው ነገር ማድረግ ብቻ ነው። እዚ  መጥተን የተቀበለንም የደገፈንም ለኛም ለነሱም እኩል ነው። እንደውም ብልጫ በነበረን ሰዓት የኛ ድጋፍ ይበልጣል። ይሄ ለሌሎችም ትምህርት ነው። ሌላ ክለብም ልክ እንደኛ አቀባበል ይጠብቀዋል ብየ አስባለው። የትኛውም ቦታም  መኖር አለበት ባይ ነኝ።

” ከባዱ ነገር ይሄን መስበር ነበር። ክለባችንም ይህንን በጨዋነት ለመጫወት ፍቃደኛ ሆኖ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነው። እነሱ ደሞ እኛን የተቀበሉበት መንገድ ሌላ ደስ የሚል እና አስተማሪ ነገር ነው። ይህ በሁሉም ክለቦች መቀጠል አለበት።

” እግር ኳስ ሜዳ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በቅፅበት የሚፈጠረውን ነገር አታውቀውም። በቃ ያ የእግር ኳስ ስሜት መሆኑ ብቻ መረዳት አለብህ። ከዛ የዘለለ ነገርም ማሰብም የለብንም። የጨዋታ ልዩ ስሜት መኖር አለበት፤ ስሜቱን የሚቆጣጠረው ዳኝነት ነው። ከሜዳው ውጭ ያለው ደሞ ኮምሽነር እና የኳሱ ህግ ነው በቃ። ”


“ስብስባሻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በጉዳት እየተመናመነ ነው” ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ስለ ጨዋታው

” በፋሲል በኩል ባለፈው ከነበራቸው ስብስብ ብዙም ሳይቀይሩ ነው የገቡት። በኛ በኩል ደሞ ከግብ ጠባቂ ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾች አስቀምጠን ነበር የጀመርነው። በቂ የጨዋታ ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾች ራሳቸውን የሚያሳዩበት ዕድል ለመፍጠር አስበን ነበር የገባነው። ውጤት ይዞ መውጣት ዋና አላማችን አልነበረም። እንዳያችሁትም ጥሩ ነው፤ አንዳንድ ከሜዳ ርቀው የነበሩ ተጫዋቾቻችን እንደፈለግነው ጥሩ ብቃት ላይ ባይገኙም ባጠቃላይ ከሜዳ ርቀው እንደመምጣታቸው ጥሩ ነው።

” ስብስባሻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በጉዳት እየተመናመነ ነው። እኔ የሚሳስበኝ ይህ ውድድር አይደለም፤ ዋናው የሊግ ጨዋታ ነው። እሀድ ከወላይታ ድቻ ላለብን ጨዋታ በሚገባ እየተዘጋጀን ነው። አሁን ትንሽ ያስቸገረን ጉዳት እና ቅጣት ነው። እንዳያችሁት ጉዳት ላይ የነበረው ዋለልኝ  ገብሬ ቀይረን አስገንተን ልናየው ሞክረን ነበር፤ እሱም ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ገብቶ ተቀይሮ ወጥቷል። ”

ቀጣይ ጨዋታ እና የአማራጭ መጥበብ

” ስብስባችን በቃ ይህቺ ናት። በዚ ሶስት እና አራት ቀን ውስጥ ከጉዳት የሚመለሱልን ተጫዋቾች ካሉ ከህክምና ባለሞያችን ጋር እንነጋገራለን። ጨዋታው ከሜዳችን ውጭ እንደመሆኑም ባለን ስብስብ በተለየ የጨዋታ ስልት ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን። ”

ዛሬ ስለተሰለፉት ተጫዋቾች

” ተጫዋቾቼ አቅም አላቸው። ለረጅም ጊዜ ከሜዳ በመራቃቸው ብዙ የመሰለፍ ዕድል አላጋጠማቸውም እንጂ ብቃት አላቸው። ከሜዳ ስትርቅ የአካል ብቃት ለማምጣት ትቸገራለህ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *