የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን አራት ሀገራት ይካፈሉበታል ተብሎ በሚጠበቀውና በአስመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው “የሠላም እና የወዳጅነት ዋንጫ” ላይ እንደሚሳተፍ ፌዴሬሽኑ ማረጋገጫ ሰጠ።
በየካቲት ወር በአስመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደውና በኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ወጣት ቡድኖች መካከል በሚደረገው ‘የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ’ ላይ የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን እንደሚሳተፍ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል። የአራቱን አባል ሀገራት ወዳጅነት እና የዞኑን የእግርኳስ ትስስር ለማጠናከር ታስቦ ለመጀመርያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሚካፈል እና ከቀናት በኋላ ዝግጅት እንደሚጀምር ተነግሯል።
ትላንት በነበረው ዘገባችን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዩጋንዳ ታስተናግደዋለች በተባለው የሴካፋ ዋንጫ ላይ በበጀት እጥረት እንደማይካፈል እንደገለፅን የሚታወስ ነው። ሆኖም ዛሬ ጠዋት ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው መረጃ ከሴካፋ ውድድር ብሔራዊ ቡድን በበጀት እጥረት ሳይሆን በአስመራ በሚካሄደው የሠላም እና የወዳጅነት ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ በመሆኑ የውድድር መደራረብ በመፈጠሩ እንደማይካፈል ተገልጾልናል። ሴካፋ የውድድሩን ካላንደር በዘፈቀደ የሚያወጣ እና ውድድሩን የሚያካሂድበት ቦታ እና ጊዜ ግልፅ ባለማድረጉ ላለመሳተፉ ምክንያት እንደሆነ አሳውቋል።