ደደቢት ከኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ራሱን ማግለሉን ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ አሳውቋል።
ከፋይናንስ እጥረት ጋር እየታገለ ሊጉን ከጀመረ በኋላ በትግራይ ክልል በተደረገለት ድጋፍ መቀጠል የቻለው ደደቢት ከበርካታ ሽንፈቶች በኋላ በዘጠነኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን ማሳካቱ ይታወሳል። ይሁንና ክለቡ አሁንም የፋይናንስ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባለመፈታቱ በኢትዮጵያ ዋንጫ ለመሳተፍ እንደሚከብደው በመግለፅ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ማስገባቱን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል። አቶ ሚካኤል እንዳሉት ክለቡ ባለበት ችግር ምክንያት ከውድድሩ ራሱን ያግልል እንጂ ዘንድሮ ከመጀመሪያው አቅዶ የተነሳነውም በፕሪምየር ሊጉ ላይ ብቻ ለመካፈል ነበር። በመሆኑም አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በቀር በውድድሩ የአንደኛ ዙር ጨዋታ የደደቢት ተጋጣሚ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በቀጥታ ወደ ሩብ ፍፃሜ የሚገባ ይሆናል።
ደደቢት ባሳለፍነው የውድድር ዘመንም በተመሳሳይ ራሱን ከኢትዮጵያ ዋንጫ ማግለሉ የሚታወስ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር እና ኢትዮ ኤሌክትሪክም ተመሳሳይ መንገድን መርጠው ነበር።