ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ

የመጨረሻው የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ይሆናል። 

ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ዋንጫ ተገናኝተው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ነገ ደግሞ በሊጉ የአስረኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምስተኛው ሳምንት በኋላ ሽንፈት ባያገኘውም ከአምስቱ ጨዋታዎች ሦስቱን ያለግብ ነበር ያጠናቀቀው። ነገር ግን ካገኛቸው ሁለት ድሎች ጋር ተደምሮ የነጥብ ስብስቡ ወደ አራተኛነት ከፍ አድርጎታል። መከላከያ በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾቹን በቀይ ካርድ አጥቶ በአራት ግቦች ልዩነት ይሸነፍ እንጂ ወደ መልካም አቋም የተመለሰ ይመስል ነበር። ሦስት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት ክለቡ አሁን 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወትሮም ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዚሁ ሳምንት ተገናኝተው የነበረ ከመሆኑም አንፃር ነገ ይበልጥ እንደሚከብድ ይጠበቃል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሀሪ መና ፣ ምንተስኖት አዳነ እና ሳላሀዲን በርጌቾ በተጨማሪ የፊት አጥቂው አቤል ያለውንም በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀምም። በተመሳሳይ አቤል ማሞ እና አቅሌሲያስ ግርማ ያልተመለሱለት መከላከያ ዳዊት እስጢፋኖስን በጉዳት የሚያጣ ይሆናል።  ተመስገን ገብረኪዳን እና ዓለምነህ ግርማም በቅጣት ከነገው የጦሩ ስብስብ ውጪ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዋንጫው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለነገው ግንኙነታቸው አንዳቸው ስለሌላኛቸው ያላቸውን ግንዛቤ የሚጨምር እና ይበልጥ ለውጦችን አድርገው እንዲመጡ የሚያደርግ ነው። በጨዋታው በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫዋቾች ምርጫ ላይ ለውጦችን ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል ። ከዛ በተጨማሪ የተጋጣሚውን ቅብብሎች ካቋረጠ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ውስጥ ከሚጥላቸው ኳሶች ጎን ለጎን የጦሩ የኋላ ክፍል ከግብ ክልሉ በሚርቅባቸው አጋጣሚዎች በፈጣን ሽግግሮች ጥቃቶችን መፈፀምንም እንደ አማራጭ ሊጠቀምበት ይችላል። ይህን ለማድረግም የመስመር ተመላላሾቹ ሚና ከፍ ያለ ይሆናል። የቡድኑ የፊት አጥቂዎች የሚላኩላቸውን ቀጥተኛ ኳሶች ካወረዱ በኋላ በሳጥን ውስጥ የሚያደርጓቸው ቅብብሎች የሚፈጥሩት ክፍተትም ለቡድኑ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

በመከላከያ በኩል አምስት አማካዮችን ከመጠቀም ይልቅ በቀድመው የዳይመንድ ቅርፅ ባለው የአማካይ ክፍል መጠቀም የተሻለ እንደሆነ የጥሎ ማለፉ ጨዋታ እንዳስተማረው ይታመናል። ቡድኑ መሀል ላይ ያደርጋቸው የነበሩት ንክኪዎች ለመልሶ ጥቃት ይዳርጉት የነበረ በመሆኑም ተጋጣሚው መሀል ሜዳ ላይ የሚያሳድርበትን ጫና ረዘም ባሉ ኳሶች ማለፍ ሲያዋጣው ታይቷል። በነገው ጨዋታ የዳዊት እስጢፋኖስ አለመኖር ሲጨመርበት ደግሞ ሁለተኛው አማራጭ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል። በመሆኑም ከፊት ለሚኖሩት ሁለት አጥቂዎች የተመጠኑ ኳሶችን እየጣሉ ትክክለኛውን የማጥቂያ ጊዜ መጠባበቅ ከመከላከያ ይጠበቃል። ቡድኑ ከተጋጥሚው የመስመር ተመላላሾች ተፅዕኖ ፈጣሪነት አንፃር በሁለቱ ኮሪደሮች ለተከላካይ መስመሩ በቂ ሽፋን እንዲሰጥም ይገደዳል። ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥር ከሆነ ግን መሀል ላይ ተጫዋቾችን በማብዛት ወደ መልሶ ማጥቃቱ ማመዘኑ የሚቀር አይመስልም። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በርካታ ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ 26 ጊዜ ተገናኝተው መከላከያ ሁለት ጊዜ ብቻ ሲያሸንፍ 13 ጊዜ አቻ ተለያይተው 11 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸንፏል። መከላከያ 14 ጎሎች ሲያስቆጥር ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 አስቆጥሯል።

– ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ከሚያሳዩ እውነታዎች መካከል ካለፉት 13 ግንኙነቶች 10 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት መጠናቀቃቸው ነው።

– በ2009 የመጀመሪያ ዙር ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፈ በኋላ በሁሉም ውድድሮች በተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች መከላከያ ሦስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ሦስት ጨዋታዎች አምስት የቢጫ ካርዶችን መዟል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ  – ፍሬዘር ካሳ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ– ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

ሳላሀዲን ሰዒድ – አሜ መሀመድ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ 

ምንተስኖት ከበደ –  አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

በኃይሉ ግርማ

ሳሙኤል ታዬ – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ፍሬው ሰለሞን

ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ

                                                       

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *