ደደቢት 2-1 ወላይታ ድቻ – የጨዋታ ቅኝት


ዮናታን ሙሉጌታ


 

በ2008 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ሙሉ ሁለተኛ ጨዋታ ደደቢት ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 2- 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዓመቱን ውድድር በድል ጀምሯል፡፡ ደመቅ ባለ የተመልካቾች ብዛት የተካሄደውን የትላንቱን ጨዋታ እንደሚከተለው አቅርበንላችሁዋል ፡፡

 

የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ አቀራራብ

በመሳይ ተፈሪ የሚመራው የወላይታ ድቻ ቡድን የሚታወቅበት የ3-5-2 አጨዋወት በመሀል ሜዳ በተጋጣሚዎቹ ላይ የቁጥር ብልጫን ለመውሰድ ይረዳል፡፡ ይህንን ብልጫ ለመውሰድ ከፍተኛውን ሚና የሚወጡት ሁለቱ የመስመር ተመላላሾች (wing backs) ናቸው፡፡ በተለይም በሽግግር ወቅቶች ላይ የሁለቱ የመስመር ተሰላፊዎች የቦታ አያያዝ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ላይ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ በመከላከል ጊዜ ከሦስቱ ተከላካዮች ጋር በሁለቱም መስመሮች በመግባት ከኋላ የአምስት ተከላካዮች ቅርፅ ማስያዝ እና በማጥቃትም ጊዜ እንዳስፈላጊነቱ መስመራቸውን ጠብቀው እስከ ተጋጣሚ የግብ ክልል ድረስ በመሄድ ከአጥቂ አማካይ እና ከአጥቂዎች ጋር በመሆን የጐል አድሎችን የመፍጠር ኃላፊነታቸው በ3-5-2 አጨዋወት ላይ ወሳኝ ያደርጋቸዋል፡፡

ደደቢት ወደ ሜዳ ይዞ የገባው የ4-4-2 ፎርሜሽን ጨዋታን ወደ ጐን በመለጠጥ እና የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ከሁለቱም መስመሮች የጐል እድሎችን ለመፍጠር ይረዳል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አጨዋወት ከሁለቱ አጥቂዎች አንዱ ወደኋላ በመሳብ እና ወደ አማካዮች በመቅረብ ኳስን ለመቀበል እና ክፍተቶችን ለመፍጠር በመሞከር አጨዋወቱን ወደ 4-4-1-1 የሚቀርብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ሁለቱ የመሀል አማካዮችም አንደኛው ከተከላካዮች ፊት ለፊት በመሆን መከላከሉን እንዲሁም አንደኛው ወደፊት በመቅረብ ኳስ የማደራጀቱን ሥራ ይወጣል፡፡

የመጀመሪያ 45 የጨዋታ አጋማሽ ጨዋታው እንደተጀመረ ወላይታ ድቻዎች ወደግራ ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ደደቢት የጐል ክልል ለመግባትና ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡ ደደቢቶችም በአንፃሩ በፈጣን እንቅስቃሴ የግብ እድል ለመፍጠር ተንቀሳቅሰው ነበር፡፡ ይህም ጨዋታውን ከጅምሩ ፈጣን እና ለተመልካችም አዝናኝ አድርጐት ታይቷል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ የወላይታ ዲቻዎች የመሀል ሜዳ የቁጥር ብልጫ በሰፊው ተስተውሏል፡፡ በዚህም ዲቻዎች በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ በአማኑኤል እና ኃይለየሱስ መሪነት ኳሱን በማንሸራሸር የተሻሉ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ነገር ግን የኳስ ዝውውር ብልጫቸው ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ ዘልቆ በመግባት የጐል እድል እንዲፈጥር እምብዛም አልረዳቸውም፡፡ ይልቁንም ሙከራዎቻቸው ከደደቢት የጐል ክልል ርቀው የተገኙ ነበሩ፡፡ ለዚህም የሁለቱ የመስመር ተመላላሾቻቸው እንቅስቃሴ እንደምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ሁለቱም በማጥቃቱ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን እስከ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ድረስ በመቅረብ ለአጥቂዎቹ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጣልም ሆነ ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት ድክመት ታይቶባቸዋል፡፡ እንዲሁም ሁለቱ የደደቢት የቀኝ እና የግራ ተከላካዮች ስዩም እና ብርሀኑ ኣብዛኛውን የጨዋታ ክፍል በራሳቸው የሜዳ ክልል ላይ ማሳለፋቸው የዲቻዎችን የመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመገደብ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

ደደቢት በድቻው ግብ ጠባቂ አስራት ስህተት የታጀበውን የአመቱ የመጀመሪያውን የቅጣት ምት ጎል በ9ኛው ደቂቃ ካስቆጠረ በኋላ ድቻዎች ይበልጡን ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ ከፊት አላዛር ወደኋላ ቀረት እያለ ከበዛብህ ጋር ኳስን ለመቀበል ሙከራ በማድረግ እና በማጥቃት ጊዜ ከቴዎድሮስ ጋር በመሆን ሦስት ሆነው ይታዩ ነበር፡፡

በደደቢት በኩል የሁለቱ መስመሮቻቸው እንቅስቃሴ በቀላሉ በዲቻዎች ቁጥጥር ሥር ወድቆ ታይቷል፡፡ በእለቱ የነበሩት የመስመር አማካዮች አለምአንተና ሽመክት ይገጥማቸው ነበረውን በሦስት የወላይታ ዲቻ ተጨዋቾች የሚፈጠር የመከላከል ቅርጽ (በደደቢት ግራ መስመር ሙባረክ ሀይለየሱስ እና አናጋው በቀኝ ዘላለም ፣ አማኑኤል እና ቶማስ) አልፎ መግባቱ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር፡፡ ይህንንም ከበስተኋላቸው የሚገኙት የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት እንቅስቃሴ መገደብ ይበልጡኑ ከባድ አድርጎት ነበር፡፡

ከአራቱ አማካዮች በመሀል ሜዳ ላይ ማጥቃቱን ያግዝ የነበረው ሳምሶን ጥላሁንም እንደዚሁ በወላይታዎች የቁጥር ብልጫ እንደልቡ መንቀሳቀስ አልቻለም፡፡ ለዚህም ይመስላል አልፎ አልፎ ከሁለቱ አጥቂዎች አንዱ የሆነው ያሬድ ወደ መስመር በመውጣት እና በጥቂቱ ወደኋላ በመሳብ ኳሶችን ለመቀበል ሙከራ ያደርግ የነበረው፡፡ የደደቢት የማጥቃት እንቅስቃሴ እድሎች ይፈጠሩ የነበረውም የድቻዎቹ የመስመር ተመላላሾች በማጥቃት ተሳትፎ ላይ በሚሆኑበት ሰዓት ላይ ከበስተኋላቸው የሚኖረው ክፍተት ነበር፡፡

የሁለተኛው 45 የጨዋታ አጋማሽ የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ እንደመጀመሪያው አጋማሽ የቀጠለ ነበር፡፡ አሁንም ከርቀት ያደረጉ የጐል ሙከራዎች ቀጥለው ታይተው ነበር፡፡ በ60ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻዎች የመሀል ሜዳ ብልጫ ወደ ደደቢት ሳጥን በቅብብል የመግባት እድል ሲፈጥርላቸውም ነበር የፍጹም ቅጣት ምት አጋጣሚ የተፈጠረላቸው፡፡ የፍጹም ቅጣት ምቱንም ሀይለየሱስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር ድቻዎች ሁለት ቅያሪዎችን ያደረጉት፡፡ ቅያሪዎቹም ፀጋዬ ብርሃኑ በ በዛብህ መልዩ ዮሴፍ ዴንጌቶን በቴዎድሮስ መንገሻ ነበሩ፡፡ ከቅያሬው በኋላ ጸጋዬና አላዛር የፊት መስመሩን ሲይዙ ዮሴፍ በዛብህ ይጫወት በነበረበት ሚና ተተክቷል፡፡ በአጠቃላይ ቅያሪዎቹ በቡድኑ ላይ የጨዋታ ቅርጽ ለውጥን ያስከተሉ ባይሆኑም አጋጣሚዎች ከተፈጠሩ ጐሎችን የማግኛ አማራጭ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ ፡፡

ደደቢቶች በበኩላቸው የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ቢቀጥሉም ነገር ግን የተወሰዳባቸውን የቁጥር ብልጫ ለመቀነስ እስከ ጨዋታው መገባደጃ መዳረሻ ድረስ ቆይተዋል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ዮሐንስ ፀጋዬን በእለቱ የመስመር ጨዋታው ላይ እንቅስቃሴው ተገድቦ በታየው አለምአንተ ካሳ ምትክ በማስገባት የድቻው ዘላለም እያሱ ተጐድቶ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በማጥቃት ላይ ትቶት የሚሄደውን ክፍተት እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ መሃለኛው ክፍል በጥለቀት ሲገባ የሚተወውን ክፍተት በመጠቀም የጐል እድል ለመፍጠር የታሰበ የሚመስል ቅያሬ አካሂደዋል፡፡ በዚህም ሁኔታ የተገኘውን የግብ አጋጣሚ ሳሚ ሳኑሚ አመከነው እንጂ ቅያሬው ለደደቢቶች ጐል የሚያስገኝላቸው ሆኖ ነበር፡፡

በ80ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ሳኑሚ ከተገኘው የደደቢት ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጐል በኋላም ድቻዎች ይህንን መስመር ሰለሞን ሀብቴን በዘላለም እያሱ ቀይሮ በማስገባት ለመሸፈን ሞክረዋል፡፡ ጨዋታውን በነበረበት ውጤት ለመጨረስ ይመስላል በ82ኛው ደቂቃ ደደቢቶች ሄኖክ ካሳሁንን በያሬድ ብርሃኑ ቀይሮ በማስገባት እና ከተከላከይ ፊት ከነበረው ተስሎች ሳይመን ጐን በማጫወት በመሀል ሜዳ ላይ የነበራቸው ቁጥር በማብዛት እና ለተከላካዩ ክፍል ሽፋን በመስጠት ውጤታቸውን ለማስጠበቅ ችለዋል፡፡ ምንአልባትም ቅያሬው ከተደረገበት ጊዜ በፊት ቢቀድም ኖሮ በመሀል ሜዳው የተወሰደባቸውን የቁጥር ብልጫ መቀነስ በቻሉ ነበር፡፡

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎችም ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ጐል ለማግኘት ሲጥሩ ደደቢቶችም ተደራጅተው በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ከፊት በነበረው ፈጣኑ ሳሙኤል ሳኑሚ አማካይነት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን በጨዋታው ሌላ ግብ ሳይቆጠር ውጤቱ 2-1 እንደሆነ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ቀጥለው ሲካሄዱ ደደቢት በአዲስ አበባ ስታዲየም ንግድ ባንክን ሲገጥም ወላይታ ድቻ በሜዳው አርባምንጭ ከነማን ያስተናግዳል፡፡

 

ያጋሩ