ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ደቡብ ፖሊስ

ከነገ ጨዋታዎች መካከል ስሑል ሽረ እና ደቡብ ፖሊስ የሚገናኙበትን ጨዋታ በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ሁለቱ አዲስ አዳጊ ክለቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ሆነው የሚገናኙበት ጨዋታ 09፡00 ላይ በሽረ ስታድየም ይጀምራል። 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረዎች አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ከተሸነፉ በኋላ ነው ይህን ጨዋታ የሚያደርጉት። ምንም እንኳን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀራቸውም እስካሁን ድል ሳይቀናቸው በሊጉ በርካታ ግብ ያስተናገደ ክለብ ሆነው ነው በአደጋው ዞን ውስጥ የተቀመጡት። ሁሉንም ጨዋታዎች ያከናወነው ደቡብ ፖሊስም ከተጋጣሚው በአንድ ድረጃ ዝቅ ብሎ ይገኛል። ሣምንት በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ 1-0 የተሸነፈው ደቡብ ፖሊስ ደደቢትን ከረታበት ጨዋታ ውጪ ከድሬዳዋ አቻ ሲለያይ በሌሎቹ ሽንፈት ሲያስተናግድ ቆይቷል። ደካማ አቋም እያሳዩ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ በመገናኘታቸው ጨዋታውን በመሸናነፍ ካጠናቀቁ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድል ይኖራቸዋል።

ስሑል ሽረ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙት ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ አይመለሱም። ሸዊት የውሃንስ ፣ ሰለሞን ገብረመድህን ፣ መብራህቶም ፍስሃ ፣ ንስሃ ታፈሰ እና ሰዒድ ሁሴን በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። በደቡብ ፖሊስ በኩል ደግሞ በረከት ይስሀቅ ፣ ቢኒያም አድማሱ እንዲሁም ረዘም ያለ ጉዳት የገጠመው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለ ወደ ሽረ ያልተጎዙ ተጫዋቾች ሲሆኑ ሙሉዓለም ረጋሳም በተመሳሳይ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ጨዋታው ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ግንኙነታቸው ነው።

– ስሑል ሽረ እስካሁን በሜዳው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤት አጠናቋል። ከነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ ግብ ማስቆጠር የቻለውም ሲዳማን ባስተናገደበት ወቅት ብቻ ነው።

– ደቡብ ፖሊስ ከሀዋሳ ውጪ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ እና አንድ ጎል ይዞ የተመለሰው ከድሬዳዋው ጨዋታ ብቻ ነበር። በቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች ግን በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት ተሸንፏል።

ዳኛ

– እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቢጫ ካርድ (21) የመዘዘው ተፈሪ አለባቸው ይህንን ጨዋታ ይመረዋል። አርቢትሩ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠበትን የሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ጨምሮ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎችን ዳኝቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ

ሳሙኤል ተስፋዬ – ኄኖክ ካሳሁን

ኢብራሒማ ፎፋና – ጅላሎ ሻፊ – ልደቱ ለማ

ሚድ ፎፋና

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ዳዊት አሰፋ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ

አዲስአለም ደበበ – ኤርሚያስ በላይ – ዘላለም ኢሳያስ

መስፍን ኪዳኔ – በኃይሉ ወገኔ – ብሩክ ኤልያስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *